አገር አቀፉ የጤና አውደ ርዕይ ታዳጊዎች በጤናው ዘርፍ ለመሰማራት ራዕይ እንዲኖራቸው መነሳሳት የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፉ የጤና አውደ ርዕይ ታዳጊዎች በጤናው ዘርፍ ለመሰማራት ራዕይ እንዲኖራቸው መነሳሳት የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015(ኢዜአ)፦ አገር አቀፉ የጤና አውደ ርዕይ ታዳጊዎች በጤናው ዘርፍ ለመሰማራት ራዕይ ሰንቀው እንዲያድጉ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የጤና ሚኒስትር እና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች፣ አመራሮች እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን አገር አቀፍ የጤና አውደ ርእይ ጎበኝተዋል።
በአገር አቀፍ የጤና አውደ ርእይ ላይ መንግስት የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል በሆስፒታል፣ በጤና ተቋማት እና ጤና ኤክስቴንሽን ውስጥ የእናቶችና ህፃናት፣ የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን አገልግሎት አሰጣጥ እያደረገ የሚገኘው የልማት ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለፁት፤ አውደ ርእዩ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
መንግስት የጤናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂና ምርምር በመደገፍ የዜጎችን ጤና በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
የግሉ ሴክተር ዘርፉን በቴክኖሎጂና ምርምር በመደገፍ ረገድ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር አየለ ተሾመ አውደ ርእዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ተማሪዎች፣ የህክምና ሙያተኞችና ሌሎች ህብረተሰብ ክፍሎች እንዲጎበኙት ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህም መንግስት የዜጎችን ጤና ለማሻሻል ከጤና ኤክስቴንሽን እስከ ከፍተኛ የህክምና ምርምር ድረስ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማትና የአገልግሎት ስራዎችን ህብረተሰቡ እንዲረዳቸው ያደርጋል ብለዋል።
በጤና አውደ ርእዩ ለእይታ የቀረቡት ዘመናዊ የጤና ማሻሻያ ሥርዓት ስራን ህብረተሰቡ እና ታዳጊዎች አይተው እንደሀገር በጤናው ዘርፍ እየተሰራ ያለውን ስራ ለማስረዳት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በአውደ ርእዩ ምርትና አገልግሎትን ከሚያስተዋውቁ ባለሙያዎች መካከል በጤና ሚኒስቴር የጤና ቅብብሎሽና ቅድመ ጤና ተቋም ዴስክ ኃላፊ ሲራክ ጉግሳ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ቆንጂት ተክሉ እና ዶክተር እዮብ ካሴ አውደ ርእዩ በመንግስት ጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ህብረተሰቡ እንዲገነዘባቸው እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በመንግስት ተቋማት የሚሰጡ የተሻሉ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የጤና እና የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ለመዘርጋት እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት እንዲረዱት እንደሚያደርግም እንዲሁ፡፡
አውደ ርእዩን ሲጎበኙ ካገኘናቸው ግለሰቦች መካከል ደጉ ማሬ እና ሩት አዲስ፤ በጉብኝታቸው በመግንስት ጤና ተቋማት የሚሰጡ ጤና እና የህክምና አገልግሎቶችን መረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሰለሞን ተኩ እና ቃልኪዳን መላኩ እንዲሁ በአውደ ርእዩ መንግስት ጤና ተቋማትን በማሻሻል የዜጎችን ዘመናዊ የጤና ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
መሰል አውደ ርእይ በቀጣይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው አገር አቀፍ የጤና አውደ ርእይ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በይፋ መከፈቱ ይታወሳል፡፡