ቀጥታ፡

አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የተጠረጠሩ ሰባት አትሌቶች ጉዳያቸው እየተጣራ ነው - የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015(ኢዜአ)፦ አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የተጠረጠሩ ሰባት አትሌቶች ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ ዛሬ ከቀትር በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።


 

የባለስልጣኑ  ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል እንዳሉት አበረታች ቅመሞች መጠቀም አስመልክቶ በተደረገ ምርመራ ሰባት አትሌቶች የመጀመሪያ ደረጃ ተጠርጣሪ ሆነዋል።

በዚህም አራት አትሌቶች በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ጉዳያቸው እንደተያዘ እና የተቀሩት ሶስት አትሌቶች ደግሞ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ስራን በዋናነት በሚያከናውነው 'ወርልድ አትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት' በተባለው አካል ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

በአትሌቶቹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሂደቱ እየተከናወነ በመሆኑ በቀጣይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት አበረታች ቅመሞች በመጠቀም የሚያዙ አትሌቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ያሉት አቶ መኮንን የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ አትሌቶች ላይ ቅጣት ከማስተላለፍ ባሻገር ለዚህ አይነት ተግባር ሊገፋፏቸው የሚችሉ በዙሪያቸው በሚገኙ ባለሙያዎች ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

አትሌት አሰልጣኞች፣ ወኪሎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

እስካሁን አንድ የመድኃኒት ቤት ላይ የሶስት ወር እገዳ መጣሉን እና አንድ የጤና ባለሙያ በሕግ ቁጥጥር ስር ውሎ የፍርድ ሂደቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተዋል። 

በተያያዘም የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስቀድሞ የመከላከል እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የናሙና ምርመራዎችን በአገር ውስጥ ማድረግ የሚያስችል ላቦራቶሪ ለመገንባት ለዓለም አቀፉ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት(ዋዳ) የሚላኩ የሚያስችሉ ቴክኒካል ሰነዶች እንደተዘጋጁም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም