ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባህል በማዳበር ለዘመናት ለቆዩ ችግሮች እልባት መስጠት ይገባል-ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባህል በማዳበር ለዘመናት ለቆዩ ችግሮች እልባት መስጠት ይገባል-ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ
ቦንጋ ሰኔ 14/2015 (ኢዜአ) ፦ ዜጎች ልዩነትን በንግግር የመፍታት ባህልን በማዳበር ለዘመናት ላለመግባባት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች እልባት በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በውይይት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ለመምረጥ ያዘጋጀው መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ኮሚሽነር ሙሉጌታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባህልን በማዳበር ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡና ላለመግባባት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች እልባት መስጠት ይገባል።
ይህን ከግብ ለማድረስ እንደ ሀገር የተመሰረተው ኮሚሽን በርካታ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን አንስተው፣ የተጀመሩ ተግባራት ከስኬት እንዲበቁ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አካታች የሆኑ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና ምክረ ሀሳቦችን በመቀበል በሚመለከታቸው አካላት እልባት ለማሰጠት በገለልተኝነት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይህም በዜጎች መካከል መግባባት፣ ተቀራርቦ መስራትና መተማመን እንደሚፈጠር ተስፋ ማድረጋቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ሙሉጌታ፣ ለጠንካራ ዴሞክራሲ ሥርዓትና የሰላም ግንባታ መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
በምክክሩ ሂደት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በሁሉም አካባቢዎች ወካይ በሆነ መልኩ መድረኩን ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ በሌሎች አካባቢዎች እንደተደረገው ሁሉ በቦንጋም የውይይት ተሳታፊዎች የሚመረጡበት መድረክ መጀመሩን ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ አቅም፣ ዕውቀትና ብቃት ያላቸውን ተወካዮችን እንዲመርጡም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
የኮሚሽኑ አማካሪ ኮሚቴ አባል አቶ አሰፋ ገብረማርያም በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜ የሚከሰቱ ያለመግባባቶች የቀደምት ስልጣኔና ታሪክ እንዲሁም የመላው ጥቁሮች የነፃነት አርማ ተደርጋ የምትታየው ኢትዮጵያ እንዳታድግ ሳንካ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ያለንን ሀብት ተጠቅመን ከድህነት ለመውጣት ልዩቶችን በንግግር የመፍታት ባህል ልናዳብር እንደሚገባ ያወሱት አቶ አሰፋ፣ ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም የመድረኩ ተሳታፊዎች በጉዳዩ ላይ በአንክሮ በመወያየት የችግሮችን ምንጮች ለይቶ በማውጣትና ምክረ ሀሳብ በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በክልሉ በከፋ ዞን ከሚገኙ 12 የገጠር ወረዳዎችና አምስት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 7 ሺህ 650 የህብረተሰብ ክፍሎች ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
ከእያንዳንዱ ወረዳም 450 ተወካዮች የሚሳተፉበት መድረክ መመቻቸቱ ተገልጿል።
በዛሬው የመጀመሪያው ቀን መድረክ ከአድዮ፣ ጊምቦና ሳይለም ወረዳዎች የተውጣጡ 1ሺህ 350 የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።