ቀጥታ፡

የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን ከ60 ሺህ  በላይ  ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት  ተደርጓል-ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ

መቀሌ ሰኔ 14 / 2015 (ኢዜአ) ዘንድሮ በሚሰጠው የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት ማድረጉን  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ተማሪዎችን ለፈተናው ለማብቃት እገዛ ማድረጋቸውን ትምህርት ቤቶችና ወላጆች ተናግረዋል።

ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርታቸው በመስጠት ለፈተናው ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተማሪዎች ገልጸዋል።


 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የምዘናና ብሄራዊ ፈተናዎች ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ፍስሃ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ በነበረው ችግር የመማር ማስተማር ስራ ተቋርጦ ቆይቷል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተፈጠረ ምቹ ሁኔታን በመጠቀም በቅንጅት በተከናወኑ ተግባራት የመማር ማስተማር ስራው መጀመሩን ተናግረዋል።

ይህንኑ ተከትሎ ለዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተማሪዎችን ዝግጁ የማድረግ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በ75 ወረዳዎች ከሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ .ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

ለፈተናው የሚቀመጡ ተማሪዎች በ2012 ዓ. ም የመጀመርያ መንፈቅ ትምህርት የተከታተሉና  ዘንድሮ በተጀመረው ትምህርት ቀጥለው የተከታተሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ተማሪዎቹ ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ ጨምሮ በሌሎችም የእረፍት ጊዜያቸው በመምህራን ድጋፍ የማጠናከሪያ ትምህርት የተሰጣቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።


 

በመቀሌ ከተማ አፄዮሃንስ  አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዓለም አባይ በበኩላቸው “ተማሪዎችን ለፈተናው ዝግጁ የማድረግ ተግባራት ተከናውነዋል” ብለዋል ።

ዘንድሮ ዳግም በተጀመረው ትምህርት ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን በአጭር ጊዜ የተከታተሉ ቢሆንም “ቤተ መጻሓህፍትን ሙሉ ቀን ክፍት በማድረግና አጋዥ ትምህርት  በመስጠት እገዛ አድርገናል” ብለዋል።

በመቀሌ ከተማ ከተፈታኝ ተማሪዎች ወላጆች መካከል አቶ ሀይሉ መኮንን በበኩላቸው ልጃቸው ሙሉ ጊዜውን ለትምህርቱ ትኩረት በማድረግ ለፈተናው ዝግጁ እንዲሆን ሲደግፉት መቆየታቸውን  ተናግረዋል ።

“አጋዥ የትምህርት መጽሓፍት በመግዛት ልጄ ለፈተና ዝግጁ እንድትሆን አድርጊያለሁ” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ  ለምለም ሓጎስ ናቸው።   

ፈተናውን ለመውሰድ ከተዘጋጁ  የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በመቀሌ  ከተማ አፄዮሀንስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ መድሃንየ ኃይሉ በሰጠው አስተያየት “ከሶስት ዓመት በኃላ ለመማር በመብቃታችንና  ለፈተና ዝግጁ በመሆናችን የተሰማኝ ደስታ ወሰን የለውም” ብሏል  ።

ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ለፈተናው መዘጋጀቱን ገልፅዋል።

ሙሉ ጊዜዋን ለትምህርቷ በመስጠት ፈተናውን ለመውሰድ የሚያስችላትን ዝግጅት ማድረጓን የገለጸችው ደግሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ሄለን ሰለሞን ናት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም