መንግስት በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015 (ኢዜአ)፦ “መንግስት በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
በሱዳን ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ሰላም እና ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ ግብረ ኃይል ባለፉት ሁለት ወራት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን ዛሬ ገምግሟል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ግብረ ኃይል በእስካሁኑ ስራዎቹ ያስመዘገባቸው ስኬቶች፣ ያጋጠሙት ችግሮች እና በቀጣይ መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ላይ ውይይት አድርጓል።
በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግብረ ኃይልን በመወከል ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ሪፖርት አቅርቧል።
“መንግስት በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል” ሲሉ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል።
የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ መንግስት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እያከናወነ ያለው ወሳኝ ስራ አካል መሆኑን አመልክተዋል።