ቀጥታ፡

በምዕራብ አርሲ ዞን በመኸር እርሻ ከ484 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በዘር ይሸፈናል

ሻሸመኔ ሰኔ 14/2015 (ኢዜአ)  በምዕራብ አርሲ ዞን በመኸር እርሻ ከ484 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በዘር ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ስራ ሂደት መሪ አቶ አብዱለጢፍ  ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት ዞኑ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሜካናይዜሽንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በሰፊው እየተገበረ ይገኛል።

በአሁኑ የመኸር እርሻም ከ484 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በዘር ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

እስካሁን ባለው ጊዜም አርሶ አደሩ ማሳውን አርሶ ለዘር እያለሰለሰ መሆኑን ገልጸው፤ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ዘር የመዝራት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ዞኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚያደረገው ጥረት ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚውሉ እንደ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ ማሾ፣ ኑግ፣ የቢራ ገብስ፣ አኩሪ አተርና ሌሎችም የሰብል ዓይነቶችን በስፋት እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በተመለከተም ዞኑ ለ2015/16 የምርት ዘመን 615 ሺህ  ኩንታል ማዳበሪያ ለማስገባት አቅዶ እስከ አሁን 350 ሺህ  ኩንታሉን ወደ ዞኑ ማድረሱንና ከዚህም ለበልግና መኸር እርሻው እንዲውል ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱንም ገልጸዋል።

በዞኑ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እያለሙ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል የሻሸመኔ ወረዳ  ጉራ ቦራ ቀበሌ   ነዋሪው  አቶ መሐመድ  አህመድ እንዳሉት ለመኸር  እርሻው ጥሩ ምርት ለማግኘት 2 ሄክታር ማሳቸውን በኩታ ገጠም ዘዴ  በስንዴ እና ቦሎቄ  ለመሸፈን ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ነው።

ከአንድ ሄክታር መሬትም በስንዴ ምርት ከ40 እስከ 50 ኩንታል፤ ከቦሎቄ ምርቱ ደግሞ ከ7 እስከ 10 ኩንታል በሄክታር ለማግኘት  እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮፈሌ  ወረዳ ዋኬኔ አቦሳ ቀበሌ  ነዋሪው አርሶ አደር የሱፍ አደም በበኩላቸው በበልግ ወቅት ድንችና በቆሎ ማምረታቸውንና አሁን ደግሞ 3 ሄክታር ማሳቸውን በኩታ ገጠም ስንዴ ለመዝራት እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የማሳ ዝግጅቱ በጥሩ ሁኔታ ከተሰራም ከአንድ ሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠብቁ አርሶ አደሩ ተናግረዋል።

ዞኑ በበልግ እርሻው  60 ሺህ ሄክታር  መሬት በተለያየ የዘር ዓይነቶች ለመሸፈን አቅዶ ከዚህ ውስጥ 55ሺህ ሄክታሩን  በኩታ ገጠም እንዳለማ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም