ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ የምስረታ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ የምስረታ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። 

በመክፈቻ ስነ ስርአቱ ላይ የጤና፣ የግብርና፣ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን፣ የትምህርት፣ የኢንዱስትሪ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ፣ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴው 14 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ሲሆን በግብርና እና ጤና ሚኒስትሮች ይመራል። 

ኮሚቴው የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሂደት፣ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃልኪዳንን ለማስተባበር፣ ፖሊሲዎችን እና የሕግ ማዕቀፎችን ለመምራት መሆኑ ተገልጿል። 

በዛሬው የመክፈቻ ጉባኤም በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን መፍታት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመከላከል ላይ ያተኮረ ነው።

በ2012 ዓ.ም የተቀረጸውን የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን መርሐ-ግብር ለማሳካት 14 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በጋራ እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ቀረጻ ላይ ከ40 ተቋማት የተውጣጡ ከ120 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ነው የተገለጸው።

አጀንዳው የምግብ ዋስትናን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መከላከል ሲሆን አጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን መጨመር፣ የገጠር ኑሮን  ማሻሻል እና የግብርና ዘርፍ ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲወዳደር ማስቻል መሆኑ ታውቋል።

የምግብ ዋጋ ንረትን ማረጋጋት እና ጤናማ አመጋገብን ማበረታታት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶችን መጠበቅ ሌሎች በአጀንዳው የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም