በዞኑ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ፍትህን ለማስፈን ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ፍትህን ለማስፈን ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ
ሻሸመኔ ስኔ 14/15 (ኢዜአ)፡- የምዕራብ አርሲ ዞን አቃቤ ሕግ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ፍትህን ለማስፈን ትኩረት መስጠቱን ገለጸ።
የምዕራብ አርሲ ዞን አቃቤ ህግ የ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና ለ2016 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ ተወያይቷል።
የዞኑ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቤ ሐጂ በወቅቱ እንዳሉት በዞኑ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የፍትህ ስርዓቱ እንዲሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዞኑ ባላፉት ወራት የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራርን ከመዘርጋት ጀምሮ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት ዓመት የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ ህገወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሳተፉ፣ ሙስናና የሀገር ሀብት ምዝበራ የፈፀሙ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡና የህግ የበላይነት ዕውን እንዲሆን አቃቢ ህግ የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የዞኑ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ህዝቡ ፍትህ እንዲያገኝ እና በውሳኔው እንዲረካ ከባህላዊ ፍርድ ቤቶች ጋር በትብብር እየስራ መሆኑን ተናግረው በዚህም በዞኑ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የሚመጡ ክሶችና ቅሬታዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ11 ወራቶች 3 ሺህ 114 የክስ መዝገቦች መካከል 2 ሺህ 868 መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤቱ በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተጠረጠሩ 8 ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በቀጣይ በጀት ዓመትም የታዩ ድክመቶችን በማረም የተሻለ ሥራ ለመስራት እንቅስቃሴ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።
ከወይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር አቃቢ ህግ ኃላፊ አቶ አብዶ አደም በስጡት አስትያየት የዘርፉ አመራሮችና ፈጻሚዎች የተሻለ ስራ እየሰሩ ቢሆንም አሁንም የእውቀትና አደረጃጀት ችግር የፍትህ ዘርፍ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በሙስና የተገኘ የመንግስት ሀብት እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል።
የአዳባ ወረዳ አቃቢ ህግ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሁሴን ዲዶ፣ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው ጠንካራ የፍትህ መዋቅር ለመገንባት የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን መሆኑን ገልጸዋል።
''አዳዲስ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃሉን የመፈፀም አቅም በማጎልበት የህዝቡን የፍትህ ጥያቄ መመለስ አለብን'' ብለዋል።