የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ጥራት አሳድጓል- በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ጥራት አሳድጓል- በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነትና ጥራትን እንዳሳደገላቸው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ገለጹ።
የኢንዱስተሪ ሚኒስቴር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያየ የምርት ዘርፍ የተሰማሩ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የፈጠረላቸውን መነቃቃት በተመለከተ ቅኝት አድርጓል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ምክንያቶች ምርት አቋርጠው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ፣ በስራ ላይ የነበሩትን ጭምር በማነቃቃት በተሻለ መልኩ ማምረት እንዲችሉ ማድረጉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪን በማስተሳሰር፣ ምርትና ምርታማነታቸውን የማሳደግና ጥራትን ለማስጠበቅም ገንቢ ሚና ተጫውቷል።
የሂዩማንዌል ፋርማሲዩቲካል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የአስተዳደር ሃላፊ ንጉሴ ጉቻለ፣ ኩባንያው የተለያዩ መድሀኒቶችን አምርቶ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በማቅረብ ለጤናው ዘርፍ መሻሻል የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡ ወደ ማሊና ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ምርቱን በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መንግስት ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ ምርትና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
የብርቱ የማዳበሪያ ከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት አዝመራው በቀለ፤ ለአርሶ አደሮች ሰብላቸውን ለመሸከፍ፣ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለማከማቸት አስፈላጊ የሆነ ግብዓት እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርታችንን ከሚፈልጉ ደንበኞች ጋር ትስስር በመፍጠር ሰፊ የገበያ እድል ፈጥሮልናል ብለዋል።
ፋብሪካው ወደ ምርት ሂደት የገባው በቅርቡ መሆኑን የጠቀሱት ባለሃብቶቹ ንቅናቄው ምርታቶቻችንን በስፋት በማስተዋወቅ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ እንድናደርግ አስችሎናልም ነው ያሉት።
የፕላስቲክ ውጤቶች አምራች የሆነው የኤቨርብራይት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሰው ሀይል አስተዳደር ሃላፊ ባህሩ መስቀሉ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት አቅማቸውና የምርት አይነታቸውን እንዳሳደገላቸው ገልጸዋል።
የተለያዩ የፕላስቲክ ከረጢቶችን፣ የፕላስቲክ ወንበሮችን፣ እንዲሁም ሸራዎችን በጥራትና በብዛት ለማምረት አግዞናል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ ከ170 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማደረጉን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።