ቀጥታ፡

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015 (ኢዜአ)፦ የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን በጥቂት ወራት ውስጥ በማቋቋም ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስታወቀ፡፡                                    

አየር መንገዱ በ49 በመቶ ድርሻ የናይጀሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም ስምምነት በመውሰድ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደተናገሩት አየር መንገዱ በአህጉሪቷ አቪዬሽን ዘርፍ እያስመዘገበ ያለው ስኬት እና ትርፋማነት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የማስተዳደር ስራውን እውን በማድረግ ነው።

በዚሁ መሰረት የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎም የተለያዩ የዝግጅት ስራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን  ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱን ለማቋቋም ከናይጄሪያ መንግስትና ባለድርሻ ከሆኑ የናይጄሪያ ባለሃብቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ  ስምምነቶች መፈረማቸውን ገልጸዋል። 

በዚህም  እስከ መጪው ጥቅምት ወር የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ተቋቁሞ በረራ እንዲጀምር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

እንዲሁም ከናይጄሪያ ሲቪል አቪሬሽን ባለስልጣን ''የኤር ኦፕሬተር ሰርተፊኬት" ለመቀበል ሂደቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ወደ ስራ ሲገባም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በአቬሽን ዘርፍ ለማስተሳሰር በሚያከናውነው ስራ ላይ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ነው የተባለው።

በተጨማሪም አየር መንገዱ ከኮንጎ አየር መንገድ ጋር የነበረውን ሽርክና መልሶ ለመጀመር ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቶጎ "አስካይ አየር መንገድ"፤ ''ከማላዊ አየር መንገድ '' እንዲሁም "ከዛምቢያ ኤር ወይስ'' ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡   

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ሲቋቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፤ 5 በመቶ የናይጄሪያ መንግስት እንዲሁም የተቀረውን 46 በመቶ ደግሞ ሶስት የናይጄሪያ ባለሃብቶች እንደሚጋሩት ተጠቁሟል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም