ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር በመቀሌ ከተማ ተጀመረ

መቀሌ ሰኔ 14 /2015 (ኢዜአ)፡- ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የተሳተፉበት የ2015 የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀመረ።

የሻምፒዮና ውድድሩን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ሃይሌና  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ሽግግር ሃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ናቸው።


 

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ሃይሌ በወቅቱ  እንዳሉት ከሰኔ 14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄደው ውድድር የህዝብ ለህዝብ መልካም ግንኙነትን የበለጠ ያጠናክራል።

ውድድሩ በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር የሚሳተፉ ብስክሌተኞችን ለመምረጥ  የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ሽግግር ሃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በበኩላቸው በመቀሌ የተጀመረው የብስክሌት ውድድር በሁሉም የክልል አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ አስተዋጾ እንዳለው ተናግረዋል።

“ለዚህም ስፖርተኞች የሰላም አምበሳደር ልትሆኑ ይገባል” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የ2015 የብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር በመቀሌ እንዲካሄድ በመፍቀዱ እናመሰግናለን” ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አሰፋ ገብረስላሴ ናቸው።

“ውድድሩ ሰላማዊ ሆኖ  እንዲጠናቀቅ እንሰራለን” ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የውድድሩ ተሳታፊዎችም  “በተደረገልን አቀባበልና በዝግጅቱ ተደስተናል “ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም