ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል በዘንድሮው የምርት ዘመን 30 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ ነው - የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015 (ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል በዘንድሮው የምርት ዘመን በ1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 30 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ።

በክልሉ የድርቅ አደጋን ለመቋቋም የሚያስችል የእንስሳት መኖ ልማትና የውሃ አቅርቦት የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑም ታውቋል።

የሶማሌ ከልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፤ በክልሉ የዝናብ ስርጭቱ ዘንድሮ የተስተካከለ በመሆኑ የግብርና ልማት ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በመሆኑም በመደበኛ የመኸር እና የበጋ ወቅት በማልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የምርት ዘመን በ1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 30 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በስንዴ ምርታማነት 200 ሺህ ሄክታር መሬት ለማረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት በክልሉ የሰብል ልማት ላይ ያልነበረ አዲስ ታሪክ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የሌማት ቱሩፋት ንቅናቄ በክልሉ የሚገኘውን ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ የአርብቶ አደሩን ህይወት ማሻሻል የሚያስችል ዘመናዊ የልማት ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉንም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።  

የድርቅ አደጋን ምላሽ ለመስጠትም ቀጣይነት ያለው የቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘመናዊ የእንስሳት ሃብት ልማት አስተዳደር እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በድርቅ ተጎጂ በሆኑ በተለዩ ወረዳዎች የእንስሳት መኖ ልማት እና የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፉ አየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰት የድርቅ አደጋ በክልሉ በተለይም የእንስሳት ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም