ሶስተኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሶስተኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጀመረ
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015(ኢዜአ)፦ ሶስተኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በኢትዮጵያ የስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል።
በሻምፒዮናው ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚገኙ ስድስት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የተወጣጡ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
በሻምፒዮናው መክፈቻ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ውድድር ፣የተለያዩ የፍጻሜና የማጣሪያ ውድድሮች ጨምሮ የሜዳ ላይ አትሌቲክስ ተግባራት ይካሄዳሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ውድድሩ ተተኪ አትሌቶች የማፍራት አላማ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ማሰልጠኛ ማዕከላት አቋማቸው የሚፈተሽበት፣ አትሌቶች በክለቦች እና ማናጀሮች ለመመረጥ የራሳቸውን አቋም የሚያሳዩበት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
እስከ ሰኔ 17 ቀን 2015 የሚቆየው ሻምፒዮና ውድድሮች በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም እንደሚደረጉ ተመላክቷል።