ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነት እንዲሁም በፈልጎ ማዳን (Search and Rescue) በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ እና የደቡብ ሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ካፒቴን ሱቤክ ዴቪድ ዳዳ ናቸው።
በፊርማው ስነ-ስርዓት ላይ የደቡብ ሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካከል በጊዜያዊ ፈቃድ ይሰጥ የነበረውን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ቋሚ እንዲሆን እና ሕጋዊ ማዕቀፍ ይዘት እንዲኖረው እንደሚያደርግም ተገልጿል።
የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ደረጃዎች እና መርሆዎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማከናወን መሰረት የሚጥል መሆኑን ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ገልጿል።
ስምምነቱ በአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መንግስታት መሪዎች በጸደቀው ኢትዮጵያ በመሪነት የተቀመጠችበት እና አየር መንገዶች የተሟላ የበረራ ነጻነት በሚሰጠው የ’ያሙሱኩሩ’ ውሳኔ ድንጋጌዎች ላይ መመስረቱን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፍሪካ ገበያ ካለው የላቀ ድርሻ እና ተመራጭነት እንዲሁም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር የማገናኘት አቅም አንጻር በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል የስምምነቱ መፈረም ሁለንተናዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በቀን ሁለት ጊዜ መደበኛ በረራ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የሁለቱ አገራት የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
በተጨማሪም ተቋማቱ በፈልጎ ማዳን (Search and Rescue) ላይ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውም ተመላክቷል።