የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጌዴኦ ዞን የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች መልሶ መገንባት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጌዴኦ ዞን የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች መልሶ መገንባት ጀመረ
ዲላ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጌዲኦ ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የ10 የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች መልሶ ግንባታ ዛሬ ጀመረ።
የማህበሩ የዲላ ቅርንጫፍ የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ዳካ ማህበሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር በዞኑ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ግንባታ ጀምሯል።
በዛሬው ዕለትም በዲላ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤት አፍርሶ በመገንባት የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መጀመሩን አስረድተዋል።
ጽህፈት ቤቱ በዞኑ ከ850 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማቀፍ ያረጁ ቤቶች መልሶ ግንባታን ጨምሮ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ማህበሩ ለሚያከናውናቸው ሰብዓዊ ተግባራት የዞኑ ሕዝብ አባል በመሆን እንዲደግፍ ሃላፊው ጠይቀዋል።
ቤታቸው ለረዥም ዓመታት ጥገናና እድሳት ባለማግኘቱ ለተለያዩ ችግሮች ሲያጋልጣቸው እንደነበር የተናገሩት ወይዘሮ አሰገደች መንገሻ ናቸው።
በበጎ አድራጊ ወጣቶች ያረጀው ቤታቸው ፈርሶ በአዲስ በመገንባቱ ችግራቸውን እንደሚቃል ተናግረዋል።
በአካባቢዋ የምታስተውላቸውን ችግሮች ለማቃለል ማህበሩን ተቀላቅላ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማሯቷን የገለጸችው ደግሞ በጎ ፍቃደኛ ተማሪ አሜን ለማ ናት።
በጎ ተግባር የአዕምሮ እርካታ እንደሚያስገኝ አመልክታ፣ወጣቶች በበጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ወገናቸውን እንዲያግዙ ጠይቃለች።
የዲላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አይደፈር ሽፈራው በበኩላቸው ማህበሩ ወጣቶችን በማስተባበር በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑ ተናግረዋል።
በዚህም በከተማው የሚገኙ ወጣቶች የበጎ ተግባራት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ ሕዝቡና ተቋማት ለማህበሩ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።