ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከተሞችን ሙሉ በሙሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው-ሚኒስቴሩ

ድሬዳዋ ሰኔ 13/2015 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከተሞችን ሙሉ በሙሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የከተሞች የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ ድርጅቶችን የአገልግሎት አሰራራቸውን ማዘመን" በሚል መሪ ሃሳብ 14ተኛው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ከተሞች የውኃ አገልግሎቶች ዓመታዊ ፎረም በድሬዳዋ ዛሬ ተጀምሯል።


 

ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር አስፋው ፎረሙን ሲከፍቱ እንዳመለከቱት የአገሪቱን ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በዘመናዊ አሰራርና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተደራሽ ለማድረግ የተያዘው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።  

የአገር ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ማሳካትም ሆነ የሰው ልጅ የህልውና ዋልታ የሆነውን የውሃ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የዘርፉ አካላት ተቀናጅተው መረባረብ ወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠል የ10 ዓመታት መሪ ዕቅድ በማዘጋጀትና  ከኢትዮጵያ ከተሞች ውሃና ሳኒቴሽን ፌደሬሽን በማቋቋም፣ ከክልሎች ከከተሞች እና ከዘርፉ አጋር አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ርብርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዘርፉ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም የሚፈለገውን ዘመናዊ አሠራርና የውሃ ሃብት አስተዳደር ከማምጣት አንፃር ርብርቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

በቀጣይ 10 ዓመታት አሁን ያለውን ከ60 ነጥብ 4 በመቶ የውሃ ሽፋን ወደ 100 በመቶ ለማድረስና የዜጎችን የኑሮ መሠረት የሆነውን ውሃ ተደራሽና አገልግሎቶቹን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ከአጋር አካላት ጋር በመሆን  አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማገዝ፤ የቁልፍ ተግባራት አፈፃፀም መለኪያና ሶፍት ዌር በ17 ከተሞች ላይ ተሞክሮ የተገኘውን ውጤት በሁሉም ከተሞች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር አስፋው ተናግረዋል። 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ ድሬዳዋ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ዳር የሚደርሱት የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎቶችን በዘመናዊ መንገድ ተደራሽ በማድረግ ነው ብለዋል።


 

አስተዳደሩ  ለዜጎች የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ ከሚኒስቴሩና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የዘርፉን አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የከተሞች ውሃ ፌደሬሽን የከተሞች መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎቶች ተወዳዳሪ፤ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ አንግበው አገልግሎት የሚሰጡ በማድረግ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሀብታሙ ፋንታ ናቸው።

በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትና ለ10 ዓመታት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የተለያዩ አደረጃጀቶች፤ የዘመናዊ አሠራር ማኑዋሎችና ውጤት አምጪ አቅጣጫዎች መዘርጋታቸውን አስረድተዋል።

እነዚህን በተቀናጀ መንገድ ተረባርቦ በመተግበር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በትጋት መስራት አለብን ብለዋል።       

በፎረሙ ላይ የፌዴራል ፤የክልሎችና የከተሞች የዘርፉ አመራሮች በመሳተፋ ላይ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም