ቀጥታ፡

የአፍሪካ አየር መንገዶች የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ በጋራ ሊሰሩ ይገባል - ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አየር መንገዶች እምቅ  አቅማቸውን በመጠቀም የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር (አያታ) ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋልሽ ገለጹ።

ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር በአፍሪካ ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።


 

በመርሐ-ግብሩ ላይ የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋልሽ፤ የትራንስፓርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ተገኝተዋል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ኃላፊ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር እና የአፍሪካ አየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ የአውሮፕላን አምራቾችና ጥሪ የተደረገላቸው የዘርፉ ሙያተኞች ተገኝተዋል።

የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋልሽ፤ የአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሚጠበቀው ልክ እንዳያድግ የሚጎትቱ ማነቆዎች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።

በቂ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር እና የዋጋ ውድነት፣ ከጥቂት አየር መንገዶች ውጭ ምቹ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ አየር መንገዶችን መገንባት አለመቻሉን ገልጸዋል።

የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ፣የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን ማፋጠንና ፓሊሲ አውጪዎች በዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ማገዝ ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት ለማስተሳሰር በጋራ መስራት እንደሚገባም እንዲሁ።

አፍሪካ እምቅ አቅም ያላት መሆኑን ያነሱት ሚስተር ዊሊ ዋሊሽ፣ ማህበሩ የአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ በሚጠበቀው ልክ እንዲያድግ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ  በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በእቅዱ መሰረት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። 


 

ማህበሩ በአህጉሪቷ ያለውን የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል እየሰራ መሆኑን በማንሳት የኢትዮጵያ አየር መንገድም ቀጣይነት ላለው እድገቱ ከማህበሩ ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ  የኢትዮጵያ መንግስት ለአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዳስትሪ እድገት ከአፍሪካ መሪዎችና መሰል ማህበራት ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈጣን እድገት ላይ መሆኑን ጠቅሰው አፍሪካንና የተቀሩትን ዓለም በኢኮኖሚ እያስተሳሰረ የሚገኝ የስኬት ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።

 ጉባኤው ነገም የሚቀጥል ሲሆን፣ በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ደህንነት መሻሻል፣ የአየር ትስስርን ማጠናከር የዘመነ የአየር መንገዶች የገበያ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥና አዋጪ የሕግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡበት ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም