ቀጥታ፡

የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግር መበራከት በአገር የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ፈተና እየሆነ መጥቷል- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015 (ኢዜአ)፦የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግር መበራከት በአገር የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ፈተና እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ከታኅሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ታኅሳስ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ላይ ያደረገውን የጥናት ሪፖርት አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ ከሲቪክ ማኅበራትና የጸጥታ ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።


 

በሪፖርቱ ይፋ የተደረገው በፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራም፣ ዩ-ቲዩብና ቲክቶክ የተሠራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን ነው።

በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ማሳየትና የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች የወሰዱትን እርምጃ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ለመከላከል ጥረት እንዲያደርጉ ለማስቻል ሪፖርቱ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃዎች የአገርን ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ላይ እየጣሉ መሆኑን ገልጸዋል። 

የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሠራጩ አካላት አብዛኞቹ በማይታወቅ አድራሻ በድብቅ ቢሆንም በውጭ አገራት ከኢትዮጵያ ሕግና ሥልጣን ውጭ ሆነው የሚያሠራጩትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

በባለሥልጣኑ የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር ኤደን አማረ በበኩላቸው የግለሰብ፣ የቡድኖችና የተቋማትን ስም ለማንቋሸሽ፣ ለማሳፈር፣ ለማግለል፣ ዓላማ ያደረጉ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግሮች መሠራጨታቸውን በሪፖርቱ አመላክተዋል።


 

በምስል ሰብዓዊነትን የሚያጎድፍ፣ ማግለል፣ የከረረ ተቃርኖና ሌሎች ጉዳዮችም ላይ ትኩረት ያደረጉ የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃዎች መሠራጨታቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

የጥላቻ ንግግር በብዛት በጽሑፍና በቪዲዮ ቀርበዋል፤ በፖለቲካና ብሔር ተኮር የሆኑ የስድብ፣ የማዋረድ፣ የማንቋሸሽና ሌሎችንም ይዘቶች ያካተቱ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች መሠራጨታቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጭ ሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር መበራከት በሰብዓዊ ክብር፣ በዜጎች ሕይወትና በአገር ሁለንተናዊ ሰላም ላይ ከባድ ፈተና መደቀኑን ገልጸዋል።

የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ለተለያዩ ወንጀሎችና ለግጭቶች መነሻ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፤ የወንጀሉን ፈጻሚዎች ተጠያቂ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ፣ በመከላከልና በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የክትትልና ቁጥጥር አቅምን ማጠናከር፣ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ የግንዛቤ ሥራን ማጠናከርና ሌሎችም በምክረ-ሃሳቦች ቀርበዋል።

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል በተለይም መገናኛ ብዙኃን፣ አስፈጻሚ አካላትና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም