ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ታጠናክራለች--አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ያላትን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

የእንግሊዝ መንግስት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን የውጭ ንግድ ለማሻሻል ይፋ ያደረገው የንግድ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ አዳዲስ እድሎችን የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የንግድ ሚኒስትር ናይጅል ሁድልስተንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው የሁለቱን ሃገራት የቆየ ትብብርና የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ምቹ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር እየወሰዳቸው ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የንግድ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመለካቸው ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብሯን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የንግድ ሚኒስትር ናይጅል ሁድልስተን በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትና መንግስት እየወሰደ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀዋል።


 

የእንግሊዝ መንግስት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን የውጭ ንግድ ለማሻሻል ትናንት ይፋ ያደረገው የንግድ ፕሮግራም (Developing Countries Trading Scheme (DCTS)) በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን ላደረጉ የንግድ ተቋማት እና ኩባንያዎች አዳዲስ እድሎች እንደሚከፍቱ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ መፈራረማቸው ይታወቃል።

ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1889 ሲሆን በየአገራቱ ኤምባሲ በመክፈትም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም