ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ከነተሽከርካሪዎቹና ተጠርጣሪዎቹ ጋር መያዙን ፖሊስ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ከነተሽከርካሪዎቹና ተጠርጣሪዎቹ ጋር መያዙን ፖሊስ ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ ከ11 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ከነ-ተሽከርካሪዎቹ እና ተጠርጣሪዎቹ ጋር መያዙን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
የተለያዩ አልባሳት ቦንዳ፣ ሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች፣ የተለያዩ ዓይነት ሲጋራዎች እና ህገ-ወጥ መድሀኒቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች የተያዙት መነሻቸውን ከጂቡቲ አድርገው አዲስ አበባ ከተማ ሊገቡ ሲሉ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኅብረተሰቡ የደረሳቸውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ በጋራ ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ከነ-ተሽከርካሪዎቹ መያዛቸው ታውቋል።
በወንጀሉ የተሳተፋ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሆነ ተገልጿል።
የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጉምሩክ ኮሚሽን በደረሰኝ ገቢ መደረጋቸውም ተጠቅሷል።
የፀጥታ ተቋማቱ በኮንትሮባንድ ላይ እያደረጉ ያሉትን የተቀናጀ ኦፕሬሽንና ክትትል አጠናክረው መቀጠላቸውን እየገለጹ ኅብረተሰቡም እስከ አሁን ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ውስጥም ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።