ቀጥታ፡

6 ነጥብ 77 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች እየተሰራጨ ነው- ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015 (ኢዜአ)፦ከጅቡቲ ወደብ የተጓጓዘ 6 ነጥብ 77 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በመሰራጨት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስቴር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ለ2015/16 የምርት ዘመን 21 ቢሊየን ብር ድጎማ በማድረግ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ገዝቶ በማጓጓዝ ላይ ይገኛል።

በዚህም መሰረት በምርት ዘመኑ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመ ሲሆን 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታሉ ጅቡቲ ወደብ መድረሱ ተገልጿል፡፡

ከጅቡቲ ወደብ የተጓጓዘ 6 ነጥብ 77 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አሁን ላይ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በመሰራጨት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ተናግረዋል።

ጅቡቲ ወደብ ላይ ከተራገፈው 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል አሁን ላይ 6 ነጥብ 77 ሚሊዮን ኩንታሉ እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

የአፈር ማዳበሪያን ገዝቶ የሚያቀርበው መንግስት ብቻ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሶፊያ፤ በቀን እስከ 200 መኪና የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዘ በመሆኑ አርሶ አደሮች ከህገ ወጥ ነጋዴዎች እንዳይገዙም አስገንዝበዋል።


 

 በቂ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ በመሆኑ ምንም አይነት የአቅርቦት እጥረት የለም ብለዋል።

በመጭው አርብና ቅዳሜ 500 ሺህ ኩንታል ዩሪያና 600 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ጅቡቲ ወደብ የሚደርሱ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል።

በአጠቃላይ በዚህ ሳምንት 1 ሚሊዮን ኩንታል ዩሪያና 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ማዳበሪያ ወደብ ላይ ይራገፋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲራጅ አብዱላሂ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ የገቢና ወጭ እቃዎችን የማጓጓዝና የማስተላለፍ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ለአፈር ማዳበሪያ ቅድሚያ በመስጠት በአንድ ጊዜ 600 ሺህ ኩንታል የመጫን አቅም ባላቸው መርከቦች የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም