ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሬን በህጋዊ የመላኪያ አማራጭ ብቻ እንዲልክ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሬን በህጋዊ የመላኪያ አማራጭ ብቻ እንዲልክ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015 (ኢዜአ)፦ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ወደ አገር ውስጥ የሚላከውን የውጭ ምንዛሬ በህጋዊ የመላኪያ አማራጭ ብቻ በመጠቀም በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጠየቀ።
ዓለም አቀፉ "የቤተሰብ የውጭ ምንዛሬ መላኪያ ቀን" በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሮች ዛሬ ተከብሯል።
መርሃ-ግብሩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ዕለቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ ለቤተሰብ የሚላክ የውጭ ምንዛሬ የዜጎችን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ሚና ያበረክታል።
ዓለም አቀፍ ''የቤተሰብ የውጭ ምንዛሬ መላኪያ ቀንን" አገራት ማክበር ከጀመሩ ዓመታት ማስቆጠራቸውን ገልጸው፤ ዕለቱ የሚያስገኘውን ፋይዳ በመገንዘብ በኢትዮጵያም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ማክበር አስፈላጊ ሆኗል።
እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የውጭ ምንዛሬ ምጣኔያቸውን በተለያዩ አማራጮች ማሳደግና ኢኮኖሚያቸውን ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ለቤተሰብ የሚላከው የውጭ ምንዛሬ በቀጥታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻልም መደበኛ የመላኪያ አማራጮችን ብቻ መጠቀም የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም መደበኛ የመላኪያ አማራጮችን ይበልጥ ዘመናዊና ተደራሽ ማድረግ ላይ መንግሥት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ በመጠቆም።
በመሆኑም የዳያሰፖራው ማኅበረሰብ ወደ አገር ውስጥ የሚልከውን የውጭ ምንዛሬ በመደበኛ የመላኪያ አማራጭ ብቻ በመጠቀም በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖረው ጠይቀዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው፤ የውጭ ምንዛሬ ከልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር በእጅጉ ይቆራኛል።
በመሆኑም ዕለቱ የውጭ ምንዛሬ ያለውን ፋይዳ ለመገንዘብና የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የሚያጋጥሙ ችግሮችን አጉልቶ ለማውጣትና መፍትሔን ለማመላከትም እንደሚያግዝም አብራርተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በሕጋዊ መንገድ ከውጭ አገራት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር(ሬሚታንስ) ወደ አገር ውስጥ መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።