ቀጥታ፡

ደም መለገስ የሰውን ህይወት የማዳን ድንበር የለሽ ሰብአዊ ተግባር ነው--የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት

ባህር ዳር ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ ደም መለገስ የሰውን ህይወት የማዳን ድንበር የለሽ ሰብአዊ ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ።

20ኛው ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በባህርዳር ደም ባንክ አገልግሎት ተከብሯል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ እንደተናገሩት ደም መለገስ የሰውን ህይወት የማዳን ድንበር የለሽ ሰብአዊ ተግባር ነው።

በዚህ ድንቅ ተግባር ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ ታላቅ አክብሮት ይገባቸዋል ሲሉም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል።

የባህርዳር ከተማ ደም ባንክ የደም ማሰባሰብ ስራው ላይ ከእቅዱ በላይ በማሳካት እንደሀገር ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸዋል።

የባህር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ምክሩ ሽፈራው በበኩላቸው በተያዘው አመት ምንም አይነት የደምና የደም ተዋፅኦ እጥረት በከተማው እንዳላጋጠመ አስታውቀዋል።

የባህር ዳር ደም ባንክ በክልልም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተከታታይ አራት አመታት አንደኝነቱን አስጠብቆ እንደቆየ ተናግረዋል።


በተለይም ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በማህበር በመደራጀት ከፍተኛ የሆነ የደም ማሰባሰብ ስራ ሲሰሩ እንደነበር የገለጹት አቶ ምክሩ ለዚህም ሲባል የምስጋናና የእውቅና ሽልማት መርሃ-ግብር መዘገጀቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ደም ለጋሾች ደም የመለገስ በጎ ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው ለባህርዳር ደም ባንክ ውጤታማነት የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች፣ በቴክኖሎጂ የተደራጀ የደም ባንክ አገልግሎት መዘርጋቱና ጠንካራ አመራርና ሰራተኞች መኖራቸው በመሆኑ አረያነቱን ሌሎች ተቋማት ሊከተሉት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

የአለም ደም ለጋሾች ቀን በባህርዳር ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን ትልቅ ድርሻ ለነበራቸው አካላት የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም