ቀጥታ፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዘላቂ ሰላም በማስፈን  የክልሉን ልማት ለማሰቀጠል እየተከናወኑ ነው- የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦  በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘላቂ  ሰላም በማስፈን  ልማትን  ለማቀላጠፍ  እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ- መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን ገለጹ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን የክልሉን ሰላምና አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በክልሉ ቀደም ሲል በተለያዩ አጋጣሚዎች በተከሰቱ ግጭቶች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ መረጋጋት ተፈጥሮ የልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ርዕሰ-መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር የአካባቢውን ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ያደረገውን የላቀ አስተዋጽዖ አድንቀው ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በጸጥታና በልማት ዙሪያ ከአጎራባች ክልሎች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር  በትብብርና አብሮነት የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል። 

በመሆኑም በክልሉ  ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር የክልሉን ልማትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጭን ተቀብለውና የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው በክልሉ በተለያዩ የልማት መስኮች እየተሳተፉ መሆኑን ርዕሰ-መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በቀጣይም ከብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽንና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በክልሉ የተገኘውን ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስቀጠል በልዩ ትኩረት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በክልሉ የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ በተለይም በግብርና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሕገ-ወጥ የወርቅ ማውጣትና ዝውውርን ለማስቆም የክልሉ መንግሥት ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የማርብል እና የኮፐር ማዕድናት ክምችት በብዛትና በስፋት መኖሩን ጠቁመው፤ በዘርፉ የማልማት ፍላጎት ያላቸው ሁሉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም