ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስደተኞችን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ከህብረተሰቡ ጋር ለማስተሳሰር የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ ናቸው-የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ስደተኞችን ከተቀባዩ ማህበረሰብ ጋር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በማስተሳሰር ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ማርጋሬት አቴኖ  ገለጹ።

የዘንድሮው የዓለም የስደተኞች ቀን 'ተስፋ ከሀገር ባሻገር' በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሚገኝበት በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ማርጋሬት አቴኖ፤ ቀኑ የሚከበረው በተለያዩ ችግሮች ሀገራቸውን ለቀው በስደት ለተጠለሉ ዜጎች አጋርነትን ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለብዙ  አስርት ዓመታት በልዩ ልዩ ችግር የተሰደዱ የተለያዩ ሀገራትን ዜጎች ስትቀበልና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የጠበቀና ሰብዓዊነት የተንጸባረቀበት መስተንግዶ ስታደርግ መቆየቷን ጠቅሰዋል።

አሁንም በአፍሪካ በርካታ ስደተኞችን እየተቀበሉ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ግንባር ቀደሟ መሆኗን ገልፀዋል።

የዓለም ስደተኞች ቀን ሲከበርም ድንበር ተሻግረው ለተጠለሉ ስደተኞች እንዲሁም ለተቀባይ ማህበረሰብ ተስፋና መፍትሔ የሚሰጡ ተጨባጭ ስራዎችን በማከናወን መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ከ27 ሺህ በላይ ስደተኞች በተጠለሉበት የአይሳኢታ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በስደተኞችና በተቀባዩ ማህበረሰብ ጥልቅ መስተጋብር ለመፍጠር ያከናወነቻቸውን ስራዎች አድንቀዋል።

በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተተገበሩ ፕሮጀክቶች ስደተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ በጋራ ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ዕድል መፍጠራቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም በጤና፣ በትምህርት፣ አሳ ልማት፣ በግብርና መስኮች የተደረጉ ድጋፎች የስደተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ሁነኛ ሚና እንዳላቸው ነው ያብራሩት። 

ኤጄንሲው በቀጣይም ከመንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት ጋር በመተባበር አካታችነቱ የተጠበቀ የማህበራዊ ዋስትና እና ጥበቃ እንዲሁም ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ስራዎችን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመነሳት ስደተኞች ያላቸውን ተሰጥኦና እምቅ አቅም በማውጣት ከተቀባይ ማህበረሰብ ጋር በጋራ የሚጠቀሙበትን ዕድል ለማመቻቸት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም