ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ "የቤተሰብ የውጪ ምንዛሬ መላኪያ ቀን" ተከበረ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ "የቤተሰብ የውጪ ምንዛሬ መላኪያ ቀን" በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ተከብሯል።

መርሐ-ግብሩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።


 

በመርሐ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበራት እና አደረጃጀቶች ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


 

በመድረኩ ለቤተሰብ የሚላክ የውጪ ምንዛሬ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እና የድህነት ቅነሳ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረት መደረጉንም ተመላክቷል።

ለቤተሰብ የሚላክ የውጪ ምንዛሪ የቤተሰቦችን ሕይወት ከመቀየር ባሻገር ለአገር እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የውጪ ምንዛሪን ለመላክ ያሉ አማራጮችና እድሎች የሚያሳዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በተለያዩ የዓለም አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጪ ምንዛሪን በመደበኛ አማራጮች በመላክ እያበረከቱት ያለውን የዜግነት ኃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።

በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በሕጋዊ መንገድ ከውጭ አገራት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር(ሬሚታንስ) ወደ አገር ውስጥ መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 4 ቢሊዮን ዶላር ከሬሚታንስ ለማግኘት በዕቅድ መያዙም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም