የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በማህበራዊ ሚዲያ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግር ላይ ያደረገው ጥናት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በማህበራዊ ሚዲያ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግር ላይ ያደረገው ጥናት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በማህበራዊ ሚዲያ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እና የጥላቻ ንግግር ላይ ለአንድ ዓመት ያደረገውን የጥናት ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ባለስልጣኑ በሪፖርቱ ላይ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።
ጥናቱ በፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብ፣ እና ቴሌግራም ላይ ትኩረት አድርጎ ከታህሳስ 23 ቀን 2014 እስከ ታህሳስ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የተዘጋጀ ነው።
በሪፖርቱም ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ሕዝብን ዋና ዓላማ ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች በማህበራዊ ትስስር ገጾች መሰራጨታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር ኤደን አማረ፤ የጥላቻ ንግግር በዓለም እንዲሁም በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ጠርዝ የመያዝና ዋልታ ረገጥ እሳቤ፣ የማዋረድና በማንቋሸሽ፣ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ከብሔርና ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ ይዘት ያላቸው የጥላቻ ንግግሮች በምስልና በጽሑፍ መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግሮቹ እና የሐሰተኛ መረጃዎቹ በዋናነት በብሔር ማንነትና በፖለቲካ ላይ ያነጣጠሩ እንደነበሩ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።
የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ምንጮችም የማህበረሰብ አንቂ ወይም አክቲቪስቶች ጨምሮ ሌሎች መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግሮች መስፋፋት፣ በሰብዓዊ ክብር፣ በዜጎች ሕይወት እና በአገር ሁለንተናዊ ሰላም ላይ ከባድ ፈተና መደቀኑን ሪፖርቱ አመላክቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ ግንዛቤ መፍጠር እና የሕግ ማዕቀፍን ማጠናከርን ጨምሮ ሌሎች በምክረ-ሀሳብነት ቀርበዋል።