ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተካሄደው ለውጥ የሀገር ሉዓላዊ የግዛት አንድነትን የሚያስጠብቅ ታላቅ ተቋም መገንባት ያስቻለ ነው - የአየር ኃይል የቀድሞ አባላት

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተካሄደው ለውጥ የሀገር ሉዓላዊ የግዛት አንድነትን የሚያስጠብቅ ታላቅ ተቋም መገንባት ያስቻለ መሆኑን የአየር ኃይል የቀድሞ አባላት ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቋሙን በሰው ኃይል በማብቃት፣ በቴክኖሎጂ በማዘመንና ምቹ ከባቢን በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአየር ኃይል ውስጥ ለረጅም ዓመታት ማገልገላቸውን የሚገልጹት ብርጋዴር ጄነራል ኃይለሥላሴ ገብሩ፤ በአየር ኃይሉ ላይ የተደረገው ተቋማዊ ለውጥ ሀገር በተቋሙ እንድትኮራ ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

ተቋሙ አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ ከቀድሞው ጋር ፍጹም አይነጻጸርም ያሉት የቀድሞ ወታደራዊ አመራር፤ በመሰረተ ልማት እንዲሁም ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል እመርታዊ ለውጥ ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር ኃይል ምቹ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር የተከናወኑ ተግባራትም አስደናቂ ናቸው ብለዋል።

ብርጋዴር ጄነራል ኃይለሥላሴ አክለውም አየር ኃይሉ ስልጠናዎችን በአዲስ መልክና ስርዓት እያከናወነ መሆኑን ገልጸው በተቋሙ ትልቅ መሻሻል መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘመኑ የደረሰባቸውንና ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚያስችሉትን የአየር ኃይል መሳሪያዎችን በማሟላት አስተማማኝ ዘብ መሆኑን እንደተመለከቱም ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ በፊት ያለ አገልግሎት የተቀመጡና የተበላሹ ወታደራዊ ትጥቆችንና አውሮፕላኖችን በራስ አቅም የማደስ፣ የማሻሻልና በምህንድስና የመለወጥ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ለሀገር ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

ከሰባት ዓመታት በላይ በአየር ኃይል አካዳሚ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን የገለጹት መቶ አለቃ ጌታቸው ትዕዛዙ በበኩላቸው በአየር ኃይሉ ያዩት ለውጥ ኩራት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ስር የሚገኘውና የተማሩበት አካዳሚ ከ20 ዓመታት በፊት በጎበኙበት ወቅት የተግባር መማሪያዎችና ቤተ ሙከራዎች ስራ አቁመው በማየታቸው አዝነው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በተቋሙ በተካሄደው መሰረታዊ ለውጥ ከዓመታት በፊት ያስተዋሏቸው ችግሮች ተቀርፈው በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ መቶ አለቃ ጌታቸው ገለጻ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ላይ የተወሰደው የለውጥ እርምጃ የሀገርን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በአስተማማኝነት የሚያስጠብቅ ታላቅ ተቋም እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የሚተማመኑበት የሀገሪቱ የአየር ክልል ዘብና ከየትኛውም አካል የሚሰነዘር ትንኮሳን በብቃት የሚመክት ተቋም ሆኖ መገንባቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም