ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር በቴክኒክ እና ሙያ እንዲሁም በክህሎት ልማት ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር ትሰራለች--የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር በቴክኒክ እና ሙያ እንዲሁም በክህሎት ልማት ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ ልዑክ በጀርመን ሙኒክ ከተማ የስራ ጉብኝት አድርጓል።

በጉብኝቱ ላይ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በተጨማሪ በሚኒስቴሩ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ እና ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን አጋርነት እና ትብብር ለማጠናከር እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ያለመ መሆኑን ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

ልዑኩ በቆይታው ከኢንዱስትሪ መሪዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የማህበራት ተወካዮች ጋር በሰው ኃይል ልማት እና ጀርመን በምትታወቅበት የሁለትዮሽ የትብብር ስልጠና አስፈላጊነት ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጉን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በክህሎት ልማት ዘርፍ ትልቅ ሚና ያለው የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ከሙኒክ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ጋር መስራት የሚችልበት ሁኔታ ላይ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ምክክር መደረጉንም ገልጸዋል።

የትብብር ማዕቀፉ በሁለትዮሽ የትብብር ስልጠና፣ በጥናት እና ምርምር፣ በኢኖቬሽን፣ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ በማሳደግ እና በስራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ትብብሩ እንደ አገር በክህሎት ልማት ዘርፍ ለተጀመረው የሪፎርም ስራ ውጤታማነት ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም