ቀጥታ፡

ኢቢሲ በመዝናኛ የይዘት ስራዎች የነበረውን ገናና ስም መልሶ ለመትከል በትኩረት እየሰራ ነው- አቶ ፍሰሐ ይታገሱ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመዝናኛ የይዘት ስራዎች የነበረውን ገናና ስም መልሶ ለመትከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሐ ይታገሱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቅርብ በቴሌቪዥን ቻናሎቹ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የሚያስተላልፋቸውን ስድስት ድራማዎች በርካታ የኪነጥበብ ሰዎች በተገኙበት ትናንት አስመርቋል።


 

ኢቢሲ "ግራ ቀኝ" በዜና ቻናል፣ "በመሐል"፣ "እቴጌ" እና "ደርዳሬ" በመዝናኛ ቻናል "ሲምቦ" እና "ሒርኮ" ድራማዎችን በአፋን ኦሮሞ ቻናል ከሰኔ 18/2015 ጀምሮ ለተመልካች ማድረስ ይጀምራል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሐ ይታገሱ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ያፈራ ከመሆኑም በላይ ተወዳጅ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በማቅረብ ይታወቅ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከ1950ዎቹ ጀምሮ በድራማ፣ በሙዚቃ እና በስፖርት አይረሴና ግርምት ፈጣሪ የይዘት ስራዎችን ሲያሰራጭ እንደነበር ጠቅሰው፤ ሆኖም ላለፉት የተወሰኑ ጊዜያት በመዝናኛው ዘርፍ ተዳክሞ ቆይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ እየተካሄደ መሆኑን በማብራራት፤ ከዘመኑና ከሕዝቡ ፍላጎት አንጻር አዳዲስና ተወዳጅ የይዘት ስራዎችን ማምጣትም ትኩረት ተደርጎበታል ነው ያሉት።

ለዚህም በይዘት ተወዳዳሪ የሆኑ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ይዞ ወደ ሕዝብ መምጣቱን በመግለጽ፤ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ የነበረውን ገናና ስም መልሶ ለመትከል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በቅርቡ የሚጀመሩት ስድስቱ የቴሌቪዥን ድራማዎችም አዳዲስ ርዕሰ ጉዳይን የያዙ እና አንጋፋና አዳዲስ የኪነጥበብ ሰዎች የሚተውኑባቸው መሆናቸውን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያነሱት።

ኢቢሲ በቴሌቪዥን ቻናሉ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ዘመን ተሻጋሪ ልብወለድ “ፍቅር እስከ መቃብር”ን በተከታታይ ድራማነት ለሕዝብ ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ አንጻር የፊልም ስራን ጨምሮ የመዝናኛ ኢንዱስትሪው ማደግ እንዳለበት ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ኢቢሲ በዚህ ረገድ አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ የኪነ-ጥበብ ፍላጎት ለማሟላት ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፊልሞች በመላው አፍሪካ በአህጉር የሚታዩና የሚተረጎሙ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን በይዘት ረገድ አዳዲስ ስራዎችን ይዞ እንደሚመጣና ለዚህም ዘመኑን የዋጁ የስቱዲዮና የቴክኖሎጂ ማሟላት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመርሐ-ግብሩ የተገኙ የኪነ ጥበብ ሰዎች በበኩላቸው አንጋፋው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደ ወትሮው ሁሉ ለሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚስማሙና ተወዳጅ የመዝናኛ ይዘትን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት አድንቀዋል።

ለኢትዮጵያ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ማደግም ከሚዲያ ተቋሙ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም