ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስደተኞችና የተቀባይ ማህበረሰብ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለማቃለል አጋር ድርጅቶችና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦አጋር ድርጅቶች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ስደተኞችና የተቀባይ ማህበረሰብ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለማቃለል አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

የዓለም የስደተኞች ቀን 'ተስፋ ከአገር ባሻገር' በሚል መሪ ሀሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሚገኝበት በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ እየተከበረ ነው።


 

በመርሐ-ግብሩ ላይ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ፣ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሊ መሀመድ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን(ዩኤንኤችሲአር)ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ማርጋሬት አቲዬኖን ጨምሮ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ በዚህ ወቅት እንዳሉት “ቀውስ በበዛበት ዓለም ውስጥ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂ ዜጎችን ለማስተናገድ የባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ይሻል”።

በዓለም ላይ ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ ከአገራቸው መሰደዳቸውን ገልፀው፤ ኢትዮጵያም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያቀረበች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባላት ውስን ሀብት ከስራ አጥነት ቁጥር ማደግ፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር ተዳምሮ ስደተኞችን በቅጡ ማስተናገድ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

ያም ሆኖ “የኢትዮጵያ መንግስት ሀብት ተትረፍርፎት ሳይሆን የሰብዓዊነትና እንግዳ ተቀባይነት እሴቱ በመሆኑ ነው” ያሉት አቶ ያዕቆብ፤ አሁንም ወደ ድንበር አልፈው ለገቡ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን ነው የገለጹት።


 

የዓለም አቀፍ ድጋፎች መጠን ግን እየቀነሰና እየተቋረጠ መምጣቱ ደግሞ በስደተኞችና በተቀባዩ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስጋት መደቀኑን አንስተዋል።

በዚህም በስደተኞች ዙሪያ ሰብዓዊ ኃላፊነትን የመጋራት ዓለም አቀፍ መርህ መሰረት አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እና የጋራ ልማት ፕሮጀክቶችን ትግበራ እንዲያጠናክር አቶ ያዕቆብ ጥሪ አቅርበዋል።

እያደገ የመጣውን የስደተኞች ቁጥር በተቀባይ ማህበረሰብ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የነበሩ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ቀን በመላው ዓለም ዛሬ ታስቦ እየዋለ ሲሆን ኢትዮጵያም የዓለም የስደተኞች ቀንን ከእ.ኤአ. አቆጣጠር 2001 ጀምሮ እያከበረች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም