ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን ድጋሚ የተካሄደው የህዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት ሰኔ 19 ቀን 2015 ይፋ እንደሚደረግ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

ሶዶ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን በትናንትናው እለት ድጋሜ የተካሄደው የህዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት ሰኔ 19 ቀን 2015 ይፋ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በወላይታ ዞን በድጋሚ የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ህዝበ ውሳኔው በተደረገው ቅድመ ዝግጅት መሰረት በሰላም መጠናቀቁንም ነው የገለጹት።

በህዝበ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላጋጠሙ መጠነኛ ችግሮች ተገቢ መፍትሄ በመስጠት መራጮች መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መደረጉን ሰብሳቢዋ ትላንት ምሽት በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

የህዝበ ውሳኔው የመጨረሻ ውጤት በተያዘው እቅድ መሰረት ሰኔ 19 ቀን 2015 ይፋ እንደሚደረግ የገለጹት ሰብሳቢዋ ከተቻለም አስቀድሞ ለመግለጽ ቦርዱና ሰራተኞቹ በትጋት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

ሰብሳቢዋ በመግለጫቸው እንዳሉት በዞኑ በድጋሚ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የተሳካ እንዲሆን ቦርዱ በሰው ሀይልና በሎጂስቲክስ በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር ገብቷል።

የህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባና የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት በተመሳሳይ ሰዓት የሚካሄድ በመሆኑ ለስኬቱ የምርጫ ማዕከላትና ጣቢያዎችን የማስፋት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ከዚህ ቀደም ከነበረው የምርጫ ማእከላትን ከስምስት ወደ 12 እንዲሁም 1 ሺህ 112 የነበሩትን ምርጫ ጣቢያዎች ወደ 1 ሺህ 812 በማሳደግ ሂደቱ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

"9 ሺህ 60 የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመልምለውና በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸው ሂደቱን አስፈጽመዋል" ብለዋል።

የድምጽ አሰጣጡ መደበኛ ሰዓት ከተጠናቀቀ በኃላ መብታቸውን መጠቀም የሚገባቸው መራጮች ሰልፍ ላይ ስለነበሩ በህጉ መሰረት ለአንድ ተጨማሪ ሰዓት በማራዘም መከናወኑን ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም የምርጫው ሂደት ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የሚታዘቡ ከሀገር ውስጥ ሁለት ተቋማት ከቦርዱ ዕውቅና ተሰጥቷቸው 168 ታዛቢዎችን አሰማርተው ሂደቱን መታዘባቸውን ገልጸዋል።

በዕለቱ የመራጮች ምዝገባና የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተመሳሳይ ሰዓት መከናወኑን ያነሱት ሰብሳቢዋ በዚህም ቦርዱ ተግባሩን በሚያከናውንበት ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።

ከችግሮቹ መካከልም በብዙ ጣቢያዎች በአካባቢው ስድስት ወር መኖራቸውን የሚያረጋግጥ የህግ ቅድመ ሁኔታ የማያሟላና ህጋዊ መታወቂያ ሳይኖራቸው ድምፅ ለመስጠት የመጡ መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በቦርዱ ህግና መመሪያ መሰረት የመራጮች የመምረጥ መብታቸው እንዲጠበቅ በማሰብ ነዋሪነታቸውን በሶስት ምስክርና በሌሎች ሰነዶች በማረጋገጥ መፍትሄ በመስጠት እንዲሳተፉ መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ከ18 ዓመት በታች የሆኑ መራጮች መገኘታቸው ሌላው ችግር እንደነበር አንስተው "ግለሰቦቹ ህጉ ስለማይፈቅድላቸው እንዳይሳተፉ ተደርጓል" ብለዋል።

በተጨማሪም በሶዶ ዙሪያ በሚገኝ ድልቦ አውጥሮ 1 ምርጫ ጣቢያ ላይ ድምፅ ለመስጠት የመጣ አስፈጻሚ ባዶ መታወቂያ እየሞላ ሲያድል እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።

"በሁምቦ ምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ ሳይሆን ነኝ በሚል ባጅ አንጠልጥሎ ለመግባት የሞከረ ግለሰብ መያዙንና እንዲሁም በገሱባ 01 ምርጫ ጣቢያ አምስት ስርዝ ድልዝ ያለበት የነዋሪነት መታወቂያ ይዘው የተገኙ ግለሰቦች እንዲመለሱ ተደርጓል" ብለዋል።

ከፍተኛ የሆነ ጥሰት ሳይገኝ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሰላማዊ ሁኔታ ተከናውኖ መጠናቀቁን ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም