ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር(አያታ) በአፍሪካ ላይ ያተኮረውን ጉባኤ በኢትዮጵያ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 13 /2015(ኢዜአ):-ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር(አያታ) በአፍሪካ ላይ ያተኮረውን ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ማካሄድ ጀምሯል።

“የአቪዬሽን ዘርፉን አቅም መጠቀም” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ጉባኤ በአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ያሉ እድሎች እና ፈተናዎች ላይ ይመክራል።


 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋልሽ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ የአቪዬሽን ዘርፍ መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች፣የአውሮፕላን አምራቾች፣ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የአየር መንገድ ማህበራት፣የዘርፉ የመንግስት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ደህንነት በማሻሻል፣አዋጪ የሕግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት፣የአየር ትስስርን በማጠናከር፣የዘመነ የአየር መንገዶች የገበያ አገልግሎት አሰጣጥ፣መሰረተ ልማት እና አቅም ግንባታ፣የሰለጠነ ሰው ኃይል ማፍራት እና ሌሎች በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በጉባኤው ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ተገልጿል።

ጉባኤው እስከ ነገ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም