ቀጥታ፡

14ተኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ከተሞች የውኃ አገልግሎቶች ፎረም በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው

ድሬዳዋ ሰኔ 13/2015(ኢዜአ)፦ 14ተኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ከተሞች የውኃ አገልግሎቶች ፎረም በድሬዳዋ እየተካሄደ ይገኛል።

ፎረሙ በከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሳንቴሽን ጉዳዮች እና በዘላቂ መፍትሄዎች ላይ በመምከር አቅጣጫዎች የሚያስቀምጥ መሆኑም ተመላክቷል።


 

በውይይቱ ላይ በከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን በተሻለ እና በተደራጀ መንገድ ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት በተሞክሮነት ይቀርብበታል።

ከመድረኩ የሚገኙ የተሻሉ ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ለማስፋት ፎረሙ አስተዋጽኦ እንዳለው የኢትዮጵያ ከተሞች የውኃ አገልግሎት ፎረም ፀሐፊ አቶ ቡሽራ መሐመድ ተናግረዋል።

አቶ ቡሽራ ለኢዜአ እንደገለጹት አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ከተሞች የውኃ አገልግሎቶች ፎረም በከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ዛሬ በተጀመረው እና በቀጣይ ለተሻለ ስራ ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት ፎረም በድሬዳዋ ከተማ በዘርፉ የተሠሩ ስራዎችን እንደሚጎበኙም ገልጸዋል።

በፎረሙ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እና የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልሎች የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም