ቀጥታ፡

የሚሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ሊቲየምን የሚተካ አማራጭ አገኙ

ሰኔ 13/2015(ኢዜአ) የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ የሚያገለግለው ሊቲየምን የሚተካ አማራጭ ማግኘታቸውን አስታወቁ።

ዘ-ኩል ዳውን የተሰኘ የሳይንስ ድረ-ገጽ እንዳመለከተው በዩኒቨርሲቲው የቁሶች ፈጠራ ማዕከል ተመራማሪዎች ሸርጣን (ክራብ) እና ሎብስተር ከመሳሰሉ የባህር ውስጥ እንስሳት ዛጎሎች ውስጥ ቺቲን የተሰኘ ውሁድ መገኘቱን ይፋ አድርገዋል።

ቺቲን ከዚንክ ጋር ሲዋሃድ ደግሞ የተሻለ የባትሪ ኃይል ማስገኘት እንደቻለ ነው ተመራማሪዎች የገለጹት፡፡

ዛጎሎቹ በከተማዋ ባሉ ሬስቶራንቶች ለመግብነት ከዋሉ በኋላ የሚጣሉ ሲሆን ተመራማሪዎቹ እነዚህን ተረፈ ምርቶች በመጠቀም ከፍተኛ አቅም ያለው ባትሪ ማምረት እንደሚቻል አረጋግጠዋል።

ሊቲየም-አዮን በሞባይል ስልኮች እና ላፕቶፖች ውስጥ በብዛት የሚገኝ ሲሆን ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ለመበስበስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዓመታት እንደሚውስድበት ጥናቶች ያሳያሉ።

ይህ ደግሞ ከአካባቢ በክለት አኳያ ሲታይ ጉዳቱ የበዛ እንደሆነ ነው የሚነገረው።

በአንፃሩ ከቺቲን የሚመረተው ሊቲየም ግን አገልግሎቱን ሲጨርስ በአምስት ወራት ውስጥ ወደ ብስባሽነት በመቀየር ራሱን ከአፈር ጋር በቀላሉ የሚያዋህድ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

የቺቲን-ዚንክ ባትሪዎች ከ400 ሰዓታት በላይ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላም ከ99 በመቶ በላይ ያለምንም እንከን አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው ጥናቱ አረጋግጧል።

ዓለም እንደ ሚቴን ጋዝ እና የድንጋይ ከሰል ከመሳሰሉ በካይ የኃይል ምንጮች ከብክለት ወደ ጸዱ ምንጮች በምታደርገው ሽሽግር የቺተን ዓይነት ሰፊና በቀላሉ የሚገን እንዲሁም ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ባትሪዎች ያስፈልጋታል።

አሁን አሁን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪዎች ውስጥ አስፈላጊና ወሳኝ አካል ሆኖ የሚያገለግለው የሊቲየም ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።

ዚምባብዌ፣ ናሚቢያ፣ ጋና፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ማሊን ጨምሮ በአፍሪካ በብዛት የሊቲየም ክምችት የተገኘ ሲሆን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ደግሞ ቀዳሚ አምራች አገር ናት።

የሊቲየም ዋጋም አይቀመሴ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የቻይና እና አሜሪካ ዓይነተኛ የንግድ ፉክክር ስበት እየሆነ መጥቷል።

እንደ ፈረንጆቹ የጊዜ ቀመር በ2021 ዓለማችን 540 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሊቲየም ያመረተች ሲሆን  የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ትንበያ እንደሚያመላክተው ከሆነ ግን በ 2030  ይህ ፍላጎት ከ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ይደርሳል።

ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የተነገረለት ግኝቱ ለሊቲየም ማዕድን የሚደረገውን የአሜሪካና ቻይና ብርቱ ፉክክር ያረግበው እንደሆን ለማየት ብዙዎቹ ተስፋቸውን ሰንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም