የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በወላይታ ዞን የተካሄደው ዳግም ህዝበ ውሳኔ መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በወላይታ ዞን የተካሄደው ዳግም ህዝበ ውሳኔ መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ
ሀዋሳ ሰኔ 12/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ በወላይታ ዞን የተካሄደው ዳግም ህዝበ ውሳኔ መጠናቀቅን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በወላይታ ዞን የተካሄደው ዳግም ህዝበ ውሳኔ በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።
ቦርዱ በዚህ ህዝበ ውሳኔ ሊያሳካ ያቀዳቸው ቁልፍ ተግባራት በአብዛኛው መሳካታቸውንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
በዞኑ በ1 ሺህ 812 ምርጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ህዝበ ውሳኔ በመደበኛው 12:00 ሰዓት ላይ ያልተጠናቀቁባቸው ጣቢያዎች በመኖራቸው በቦርዱ ውሳኔ ለተጨማሪ ሰዓታት እንዲቆይ መደረጉንም አስረድተዋል።
ከምሽቱ 1ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ በሁሉም ጣቢያዎች በሚባል ደረጃ የድምጽ መስጠት ሂደቱ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
በሰዓቱ በሁሉም ጣቢያዎች ላይ ወረፋ የያዙም ሆኑ የተመለሱ ድምፅ ሰጪዎች እንዳልነበሩም ጠቅሰዋል።
በሂደቱ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በሚኖሩበት አካባቢ ለስድስት ወራት መቆየታቸውን የማያሳይ መታወቂያ በመያዝ ድምፅ ለመስጠት የመጡ መራጮች እንደነበሩ ጠቅሰው ምስክሮችንና ተጨማሪ ሰነዶችን በማቅረብ ድምፅ እንዲሰጡ በማድረግ መፍትሔ መሰጠቱን ገልፀዋል።
ባዶ መታወቂያዎችን በመያዝ ለነዋሪዎች በማደል እና አስፈፃሚ ሳይሆኑ ነኝ ብሎ ጣቢያዎች ላይ በመቅረብ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች መኖራቸውንም ሰብሳቢዋ ጠቅሰዋል።