የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ብድር እንዲሰጡ የወጣውን መመሪያ በአግባቡ ሊተገብሩ ይገባል-ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ብድር እንዲሰጡ የወጣውን መመሪያ በአግባቡ ሊተገብሩ ይገባል-ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2015(ኢዜአ)፡- የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ብድር እንዲሰጡ የወጣውን መመሪያ በአግባቡ ሊተገብሩ እንደሚገባ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ።
ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ብሔራዊ ባንክ በጋራ ያዘጋጁት የግብርና ፋይናንስ ወርክሾፕ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በዚሁ ወቅት፤ በግብርናዉ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የሚቀርበዉ የፋይናንስ ድጋፍ አነስተኛ እንደነበር ጠቁመዋል።
የግብርናዉ ዘርፍ የዉጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ በፋይናንስ መደገፍ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ብሔራዊ ባንክም የፖሊሲና የመመሪያ ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሰረት የዋስትና መብት አዋጅ ቁጥር 1147/2011 ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና መበደር የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን ጠቅሰዋል።
መመሪያው ባንኮች በዓመት ውስጥ ከሚያበድሩት ገንዘብ አምስት በመቶውን ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች ጭምር በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ የብድር ዓይነት እንዲያውሉ ያስገድዳል ብለዋል።
ይኸውም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በቂ ፋይናንስ ተበድረው ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ የማድረግ ዓላማ ቢኖረውም የፋይናንስ ተቋማቱ መመሪያውን በአግባቡ እየተገበሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም ባንኮች መመሪያውን በአግባቡ መተግበር እንዲጀምሩና በተንቀሳቃሽ ንብረት ብድር እንዲሰጡ አሳስበዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የግብርናው ዘርፍ የፍጆታ ምግቦችን ከማቅረብ ባለፈ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት መሆኑን ተናግርዋል።
ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ አበርክቶው የጎላ መሆኑን በማንሳት፤ እሴት ለሚጨመርባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች ትልቅ ግብዓት መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ አሁንም ያልተነኩ እምቅ ሃብቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ ያለውን ከፍተኛ የውሃ፣ የመሬት እና የሰው ሃብት በመጠቀም የተሻለ ማምረት እንደሚገባም ነው ያብራሩት።
መንግስት ለዘርፉ ዕድገት እየሰራ ቢሆንም፤ የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ የሚያቀርቡት ብድር አሁንም አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ብሔራዊ ባንክም አርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ ቋሚ ተክሎቹን፣ ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን እንዲሁም መሬት አጠቃቀም መብት ደብተሩን አስይዞ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ሁሉም ባንኮች ከሚያበድሩት ብድር አምስት በመቶውን ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ ለዩኒየኖች፣ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲያበድሩ መመሪያ ቢያወጣም ትግበራው አነስተኛ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣ መሰረት ብድር አግኝተዋል ተብለው የሚጠቀሱትም ጭምር በተሸከርካሪ እና በማሽነሪዎች ማስያዣ መሆኑን አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡
የአርሶ አደሮች ንብረት በሆኑት ቋሚ ተክል፣ እንስሳት፣ የመሬት የመጠቀም መብቱን ጨምሮ እህልን በማስያዝ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ አለመሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍና ለመመሪያው ተግባራዊነት ከብሔራዊ ባንክ ጋር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው አሁን ያለው የባንኮች አሰራር ለአርሶ አደሮች ምቹ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ባንኮች አሰራራቸውን ለግብርናው ዘርፍ ምቹ በሚሆን መልኩ ሊፈትሹ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንርፕራይዞች እና አርሶ አደሮች የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የወረቀት ዋስትና በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም የዘርፉ ተዋንያን ከባንኮች ብድር የሚያገኙበትን የገንዘብ ዋስትና ማስያዣ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ ለሀገር ከ60 በመቶ በላይ የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዘርፍ ቢሆንም የሚቀርብለት የብድር አቅርቦት ከ8 በመቶ በታች ብቻ መሆኑ በወርክሾፑ ላይ ተገልጿል፡፡
በወርክሾፑ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮችና ተወካዮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡