ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን እየተካሄደ በሚገኘው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ እስከ ስድስት ሰዓት 370 ሺህ 552 መራጮች ድምፅ ሰጥተዋል- ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2015 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን እየተካሄደ በሚገኘው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ባለው ጊዜ 370 ሺህ 552 መራጮች ድምፅ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ በወላይታ ዞን እየተካሄደ የሚገኘው የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ አስመልክቶ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚከተለው ነው፦

የወላይታ ዞን የድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ የድምፅ መስጠት ሂደት ዛሬ ማለዳ 12፡00 ተጀምሯል።

ቦርዱ የድጋሚ ሕዝበ ውሳኔውን የሚያከናውኑ የምርጫ አስፈፃሚዎችን በተለያየ መንገድ የመለመለ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 5 ሺህ 215 የምርጫ አስፈፃሚዎች እና ከወላይታ 3 ሺህ 845 የምርጫ አስፈፃሚዎች ተሳትፈዋል።

በዛሬው ዕለት ሁሉም አስፈፃሚዎች በሥራ ላይ ተሰማርተው መራጮችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ።

አንዳንድ ሰልፎች የበዙባቸው ጣቢያዎች ላይ ቦርዱ አሰልጥኖ በተጠባባቂነት የያዛቸውን አስፈፃሚዎችን አሰማርቷል።

በ1812 የምርጫ ጣቢያዎች የተሟላ የምርጫ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን ቦርዱ አረጋግጧል።

ከጠዋት 12፡00 ሰዓት እንከ 6፡00 ሰዓት በተገኘው መረጃ 370 ሺህ 552 መራጭ ድምፅ ሰጥቷል።

በተያያዘም የድምፅ መስጠት ሂደት ቦርዱ ለሦስት የሀገር ውስጥ ተቋማት የታዛቢነት እውቅና ሰጥቶ በዞኑ የተለያዩ ጣቢያዎች ላይ 214 ታዛቢዎች ተሰማርተዋል።

የድምፅ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በርከት ያሉ መራጮች ከተሠጣቸው 6 ወር ያልሞላው መታወቂያ ሆኖ ተገኝቷል። ነገር ግን የቦርዱ መመሪያ አንድ ዜጋ ድምፅ መስጠት የሚችለው በመኖርያ ስፍራው ቢያንስ ለስድስት ወር እና ከዚያ በላይ መኖሩ መረጋገጥ እንዳለበት ተጠቅሷል።

ስለዚህ እነዚህ መራጮች ከያዙት የነዋሪነት መታወቂያ በተጨማሪ ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጡበት የሶስት ሰዎች ምስክርነት ወይም ሌሎች የሠነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም