በአውሮፓ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት “ገበታ ለትውልድ”ን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአውሮፓ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት “ገበታ ለትውልድ”ን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2015(ኢዜአ):-በአውሮፓ አገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት “ገበታ ለትውልድ”ን ጨምሮ ለተለያዩ አገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ያላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።
በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ በጣልያን፣ግሪክ፣ማልታ እና ቆጵሮስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እና ልማት ስራዎች ዙሪያ በበይነ መረብ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ደሚቱም ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ገለጻ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መንግስትና አገር በፈተናዎች ውስጥ ሆነው ባለፉት ዓመታት የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በግዙፍ መሰረተ-ልማት ግንባታዎችና ሌሎች መስኮች ስኬቶች መመዝገባቸውን አምባሳደሯ ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተደደር ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱንና የድህረ-ጦርነት የመልሶ ግንባታ ስራዎች በመንግስት የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ዳያስፖራው ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትን አስመልክቶ የተጀመረውን ገቢ የማሰባሰብ ፕሮግራምን ጨምሮ ለሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደሯ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ በእንግድነት የተገኙት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የግድቡን የግንባታ ሂደት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ግድቡን ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በማላቀቅ በተከናወነው ስራ የግንባታው አፈጻጸም 92 በመቶ ማድረስ መቻሉን ኢንጂነር ክፍሌ ገልጸዋል።
ዳያስፖራው ከዚህ ቀደም የሕዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ላሳየው ወገናዊነትና ባለቤትነት ምስጋናቸውን አቅርበው የግድቡ ቀሪ ስራ እስኪጠናቀቅን ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ዳያስፖራዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጨማሪ ቦንድ በመግዛት እና ለሌሎች አገራዊ የልማት ፕሮግራሞች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውም ተገልጿል።