ቀጥታ፡

በሽግግር ፍትሕ ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2015(ኢዜአ)፦ ለሽግግር ፍትሕ ሂደት ስኬታማነት የሚያግዙ የማኅበረሰብ ግንዛቤን ማስፋት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በየትኛውም መልኩ የሚከሰት ግጭትና አለመግባባት ዜጎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት የመጋለጥ ዕድላቸውን ያሰፋል።

በዚህም አለመግባባቶች የሚከሰትባቸውን ጉዳዮች በመለየት መፍትሔን ማበጀትና ማመላከት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባል ይላሉ።

የሰሜኑን የአገሪቱ ክፍል ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ዜጎችን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉን አንስተዋል።

ለዚህም ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕን በማካሄድ የተፈጠሩ ስህተቶችን ማረምን ጨምሮ ስጋቶችንም እንዲሁ ማሻሻል የግድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።

ይህንን መነሻ በማድረግ እንደ አገር የሽግግር ፍትሕ እንዲካሄድ  ምክረ-ሃሳብ ካቀረቡ ተቋማትና አካላት መካከል  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አንዱና ዋነኛው ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ  የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በአግባቡ የማስፈጸምና የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል ይላሉ። 

ሂደቱ አካታች አሳታፊና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ለማስቻል በቅድሚያ የማኅበረሰብ ግንዛቤን ማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

እስካሁን ባለው ሂደትም የሽግግር ፍትሕ  አስፈላጊነቱ የአፈጻጸም ሂደቱና ፋይዳውን በሚመለከት የማኅበረሰብ ውይይቶች ተካሂደዋል።

በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶችም ማኅበረሰቡ በሂደቱ ሊካተቱ ይገባል ያሉትን ምክረ-ሃሳብ ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

በተለይም ለሽግግር ፍትሕ አጋዥ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም በውይይቱ  ከተመላከቱ  ምክረ-ሃሳቦች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤  የሽግግር ፍትሕን በሚመለከት እየተዘጋጀ ላለው ፖሊሲ ኮሚሽኑ በግብዓትነት አቅርቦታል ይላሉ።

በቀጣይም ፖሊሲውን በማውጣትና በማዘጋጀት እየተሳተፉ ያሉ አካላት የጉዳዩን አስፈላጊነት በመገንዘብ በግብዓትነት የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችን ማካተት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጠይቀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም