የግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር ይገባል-ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር ይገባል-ዶክተር ግርማ አመንቴ
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2015(ኢዜአ):-የግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለፁ።
ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት እና ብሔራዊ ባንክ በጋራ ያዘጋጁት የግብርና ፋይናንስ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የግብርናው ዘርፍ የፍጆታ ምግቦችን ከማቅረብ ባለፈ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ አበርክቶው የጎላ መሆኑን በማንሳት፤ እሴት ለሚጨመርባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችም ትልቅ ግብዓት መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ አሁንም ያልተነኩ እምቅ ሃብቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ ያለውን ከፍተኛ የውሃ፣ የመሬት እና የሰው ሃብት በመጠቀም የተሻለ ማምረት እንደሚገባም ነው ያብራሩት።
መንግስት የግብርናው ዘርፍ እንዲዘምን በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ለመካናይዜሽን የሚያገለግሉ ከ500 በላይ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።
የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ በድጎማ እንዲቀረቡ በማድረግም ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስት ለዘርፉ ዕድገት እየሰራ ቢሆንም፤ የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ የሚያቀርቡት ብድር አሁንም አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ አቅርቦት ፈሰስ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ መውጣቱን ገልጸዋል።
ባንኮችም የፋይናንስ አቅርቦታቸውን ለማጠናከር አዋጁን በአግባቡ መተግበር እንዲጀምሩ አሳስበዋል።
በግብርና ፋይናንስ ወርክሾፑ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮችና ተወካዮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።