በወላይታ ዞን ዳግም ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጠት ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን ዳግም ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጠት ተጀምሯል
ወላይታ ሰኔ 12/2015 (ኢዜአ)፡- በወላይታ ዞን ዳግም ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጠት ተጀምሯል።
በዞኑ ዳግም ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ህዝቡ ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ እየሰጠ ይገኛል።
በዞኑ ቦዲቲ ከተማ ከሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ቦዲቲ ዶጌ ሰፈረ ሠላም 05 እና ቦዲቲ ቆርኬ 03 ምርጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ አስፈፃሚዎችና ታዛቢዎች በተገኙበት የምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጀምሯል።
እየተካሄደ በሚገኘው የዳግም ምርጫም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በህዝበ ውሳኔው ድምጽ እየሰጡ ነው።
በዚህም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በዞኑ ቦዲቲ ከተማ ቦዲቲ ቆርኬ ምርጫ ጣቢያ ሶስት ድምፅ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ በኪንዶ ኮይሻ የምርጫ ማዕከል በባይራ ኮይሻ ወረዳ ጋሌ ዋርጎ 'ሀ' ምርጫ ጣቢያ ድምፅ ሰጥተዋል።
እንዲሁም የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በዴሳ ዳሞት ወይዴ የምርጫ ማስተባበሪያ ማዕከል 1 በዴሳ ቀበሌ 01 የምርጫ ጣቢያ ድምጽ ሰጥተዋል።
በዞኑ ከጠዋቱ 12:00 ጀምሮ በድጋሚ እየተካሄደ ባለው ህዝበ ውሳኔ ሌሎች የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ሕዝቡ በዞኑ በ12 የምርጫ ማዕከላት ስር በተቋቋሙ 1 ሺህ 812 ጣቢያዎች ድምፅ እየሰጡ ነው።
በዞኑ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ክልል ስር የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ከነባሩ ክልል ጋር ለመቀጠል አልያም በአዲስ ክልል ለማደራጀት የ”ክልል እንሁን” ህዝበ ውሳኔ ተካሄዶ ነበር።
በዚሁ ጊዜ በተካሄደው የህዝበ ውሳኔ በተፈጠሩ የህግ ጥሰቶች ምክንያት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ውድቅ ማደረጉ ይታወሳል።
በመሆኑም የምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔው ዳግም እንዲካሄድ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የዞኑ ህዝብ ድምጽ እየሰጠ ይገኛል።