በጋምቤላ ክልል የወጣቶችን ሁለንታዊ ተሳትፎ በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የወጣቶችን ሁለንታዊ ተሳትፎ በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጋምቤላ ሰኔ 11/2015 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የወጣቶችን ሁለንታዊ ተሳትፎ በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
በጋምቤላ ከተማ ንቁ የወጣቶች ተሳትፎ ለሀገር ሰላም በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች ፊስቲቫል ተጠናቋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ጁል ናንጋል በፊስቲቫሉ ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት የወጣቶች ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማጠናከር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ሊፋጠን የሚችለው የለውጥና የልማት ኃይል የሆነውን ወጣት በሁሉም መስኮች በማሳተፍ መስራት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችንና ማዕቀፎችን በመቅረጽ የወጣቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ተሳትፎ በማጠናከር ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎችም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጋምቤላ ከተማ የተዘጋጀው ፌስቲቫል ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ክህሎትና ተሰጦ ለማሳየት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ የወጣቶችን የእርስ በእርስ ግንኙነትና አንድነት ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል አቶ ጁል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ለክልሉ ብሎም ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲውሉ ቢሮው የወጣቶች አደረጃጀትና ተሳትፎ የማጠናከር ስራዎችን እያከናወ ነው ብለዋል።
በፌስቲቫሉ የታደሙት ወጣቶች በሰጡት አስተያየት የፌስቲቫል ዝግጅቱ የፈጠራ ስራዎቻቸውንና ተሰጧቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በእርስ ተሞክሮዋቸውን ለመለዋመጥ ጭምር እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድ/ UNFPA/ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ባዘጋጀው ፌስቲቫል ላይ ወጣቶች የደም ልገሳ፣ ስፖርታዊ ውድድር፣ ተሰጧቸውንና የፈጠራ ስራዎቻቸውን አስተዋውቀዋል።
እግር ኳስን ጨምሮ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች አሸናፊ ለሆኑ ወጣቶች የገንዘብና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።