ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ጠንካራ ተሳትፎና ተነሳሽነት ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ጥሩ ተሞክሮ የሚሆን ነው - የአፍሪካ ሕብረት

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2015 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ጠንካራ ተሳትፎና ተነሳሽነት ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን በአፍሪካ ሕብረት የብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ዳይሬክተር ሃርሰን ኒያምቤ ተናገሩ። 

በአፍሪካ ሕብረት የብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ዳይሬክተር ሃርሰን ኒያምቤ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ያሳየችው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች በአህጉሪቱ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቀነስ አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሁሉም የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማገዝና መደገፍ እንዲሁም ተሞክሮውን መጋራት አለባቸው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረትም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በመደገፍ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወጣቶቿን ወደ ደቡብ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሌሎችም ጎረቤቶቿ በመላክ የችግኝ ተከላ እንዲያካሂዱና ልምዷን ለማካፈል ያደረገችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ሕብረት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቴክኒካል አስተባባሪ ጋትኮት ካይ፤ ኢትዮጵያ የምታራምደው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስነ-ምህዳርን በመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ ጉልህ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራር ሰጪነት እየተከናወነ የሚገኘውን የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም ተሞክሮውን ቢወስዱት መልካም መሆኑን ጠቁመዋል።

"አፍሪካዊ ወንድማማችነትን መትከል" በሚል መሪ ሃሳብ አሕጉራዊ ዲፕሎማሲ ወዳጅነትን ለማጠናከር እ.አ.አ. በ2022 በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ላይ በጎረቤት የአፍሪካ አገራት እንዲሳተፉ ተልዕኮ የተሰጣቸው ወጣቶች የተሳካ ተሳትፎ አድርገው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአፋር ክልል ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በ2ኛ ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የ2015 ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም