ቀጥታ፡

ህዝበ ውሳኔው የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - ነዋሪዎች 

ሀዋሳ ሰኔ 11/2015 (ኢዜአ) ነገ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ የተሳካ ሂደት እንዲኖረው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በወላይታ ዞን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡

   በደቡብ ክልል የሚተዳደሩበትን ክልል ለመወሰን በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ባለፈው ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ህዝበ ውሳኔ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የወላይታ ዞን ነው።

ይሁን እንጂ በዞኑ በወቅቱ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የህግ ጥሰት ተገኝቶበታል በማለት ውጤቱ ውድቅ ተደርጎ ድጋሚ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነገ የህዝበ ውሳኔው ድምፅ ይሰጣል ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎችም የህዝበ ውሳኔው ሂደት የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ፍስሃ ፀጋዬ ነገ በሚካደው ድምፅ አሰጣጥ ላይ  ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

ለዚህም የነዋሪነት መታወቂያ በመያዝ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ህዝበ ውሳኔው "ስለ መዋቅራዊ አደረጃጀታችን በራሳችን ድምፅ ውሳኔ የምናስተላልፍበት የዴሞክራሲ መገለጫ ነው" ብለዋል ፡፡

በመሆኑም በራሴ የወሰንኩትን ውሳኔ ያለ ማንም ጫና በድምፄ የማስተላልፍበት ዕድል በመሆኑ ዕድሌን ለመጠቀም ነገን በጉጉት እየተጠባበቅኩ እገኛለሁ ነው ያሉት ፡፡

ሌላው ነዋሪ አቶ ታደመ ሎሪሶ ከግል ዝግጅታቸው ባለፈ በመንደራቸው ለህዝበ ውሳኔው መሳካት አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል ፡፡

ለድምፅ መስጫ ቀን የሚያገለግሉ ድንኳኖችን በመትከልና ሌሎች ዝግጅቶች የተሟሉ እንድሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል ፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያስቀምጠው መመሪያ መሰረት ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ ታደመ፤ ሠላማዊ ሂደት እንዲኖረው በህብረት አካባቢያቸውን በመጠበቅና ሌሎች ሥራዎችን በመስራት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን ክፍል ምክትል ኃላፊ ወይዘሪት የምስራች ልየው እንዳሉት በዞኑ ባሉ 12 የምርጫ ማዕከላት ስር 1 ሺህ 812 የምርጫ ጣቢያዎች መደራጀታቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

በአጠቃላይ 9 ሺህ 60 የምርጫ አስፈፃሚዎች መመደባቸውን ገልፀው ለምዝገባና ለድምፅ አሰጣጥ ሂደት የሚሆኑ ቁሳቁሶችም ወደ ጣቢያዎች መሰራጨታቸውን አስረድተዋል ፡፡

በየአካባቢው ያለው ህብረተሰብ ድንኳን በመትከልና ሌሎች እገዛዎችን በማድረግ ቀና ትብብር እያሳየን ነውም ብለዋል ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም