ቀጥታ፡

ታዳጊዎችና ህፃናት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለእውቀትና ክህሎት እንዲያውሉት ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ሰኔ 11/2015 (ኢዜአ) ታዳጊዎችና ህፃናት የዲጂታል ቴክኖሎጂን  ለእውቀትና ክህሎት እንዲያውሉት  ሁሉም ሃላፊነቱን  ሊወጣ ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

በአፍሪካ ለ33ኛ በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ የተከበረው የአፍሪካ ህጻናት ቀን የማጠቃለያ መርሀ ግብር በዛሬው እለት ተካሂዷል። 


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ሚኒስቴሩ  የህጻናትን ስብዕና ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ታዳጊዎችና ህፃናት የዲጂታል ቴክኖሎጂን  ለእውቀትና ክህሎት እንዲያውሉት ቤተሰብና ባለድርሻ አካላት   ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ  ሚንስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ፤ የዘንድሮ የአፍሪካ ህጻናት ቀን በህጻናት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ በማተኮር መከበሩን ገልፀዋል።


 

በኢትዮጵያም "ሰላም ፍቅር እንክብካቤና ጥበቃ ለሁሉም ህጻናት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል ብለዋል።

ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በህፃናት ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ከቤተሰብ ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ህጻን ቅዱስ ሞላ፤ እለቱን መሰረት በማድረግ ህጻናት ቴክኖሎጂን በምን አግባብ መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መልእክቶች መተላለፋቸውን ገልጿል።

በዚህ ረገድ በፓርላማው  ጭምር ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግሯል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኘው ተማሪ አብርሀም ሲሳይ፤ ቴክኖሎጂን ስንጠቀም ጊዜ በሚያባክኑ ሳይሆን እውቀት ሊያስጨብጡ በሚችሉት ላይ መሆን አለበት ብሏል።

በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት እስከ 17 ዓመት ከሆኑ አራት ህጻናት መካከል አንዱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በእለቱም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን በጉዲፈቻ ማሳደግ ለሚፈልጉ ቤተሰቦች አስረክበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም