ቀጥታ፡

ለ2ኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ስኬታማነት የነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2015 (ኢዜአ) ለ2ኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ስኬታማነት የመዲናዋ ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

ከንቲባዋ ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመዲናዋ በዛሬው እለት አስጀምረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞች ሲተከሉ ከዚህ ውስጥ በመዲናዋ ለውበትና መናፈሻ፣ ለምግብነትና ለጥምር ደን የሚያገልግሉ 41 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

በመሆኑም በመጀመሪያ ምዕራፍ የተመዘገበውን ስኬት በመሰነቅ ለሁለተኛው ምእራፍ ስኬትም ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት በመዲናዋ 17 ሚሊየን የውበትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ጠቁመው አጠቃላይ ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት የነዋሪዎች ሁለንተናዊ ትብብርና ተሳትፎ እንዲቀጥል ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት፣ ማህበራዊ ተቀባይነትና አካባቢያዊነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 40 በመቶ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ የዜጎች ተሳትፎ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 6 ነጠብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በከተሞች በመንገድ አካፋዮች፣ በመሰረተ ልማቶች አካባቢ የሚተከሉ ችግኞችም ለከተማ ውበት፣ ለአካባቢ እና ለጤና ተስማሚ መሆን አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።

የከተማዋ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ጀማሉ ጀንበር፤ በተያዘው ዓመት በአረንጓዴ ዐሻራ ከ17 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በምሃ ግብሩም ለሌማት ቱሩፋት አጋዥ የሆኑ የፍራፍሬ፣ አገር በቀል የጥላ ዛፍ እና የውበት ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተሳተፉት ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በ"ነገን ዛሬ እንትከል!" ሁለተኛው ምዕራፍ 5ኛ ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይነትም በመትከልና በመንከባከብ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁለተኛውን ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት ''ነገን ዛሬ እንትከል'' የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአፋር ክልል ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በሁለተኛ ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የ2015 ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዘግጅት መደረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም