ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው-ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እያደረገች ያለው ጥረት የሁሉንም ድጋፍ የሚሻና የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየሰራች መሆኑን ማረጋገጫ ነው ተብሏል።

የዓለም አቀፉ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ኦኬችኩ ኦግቦናያ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም የጀመረችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ልማትን ከ10 ዓመት መሪ የልማት አቅድ ጋር በማስተሳሰር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እያከናወነችው ያለው ስራ ለቁርጠኝነቷ ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በፖሊሲና ትግበራ ብቻ ሳይሆን የአረንጓዴ ልማትን በተቀናጀና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ማከናወን ውጤት እንደሚያመጣ የገለጹት ተወካዩ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ጥረት አድንቀዋል።


 

ኢትዮጵያ እኤአ በ2030 የካርበን ልቀትን በ68 ነጥብ 8 በመቶ ለመቀነስ ያለመች ሲሆን እኤአ በ2050 ደግሞ ወደ ዜሮ ለማውረድ አቅዳ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የረጅም ጊዜ-ዝቅተኛ የካርበን ልቀት የመቀነስ ስትራቴጂን ዓለም አቀፉ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተወካዩ ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ የቴክኒክ ምክረ-ሀሳብ መስጠት ብቻ ሳይሆን የተሻሉ ተሞክሮዎችንና ግንኙነቶችን በመፍጠር በኩል እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በማከናወን የጀመረችው ጥረት ለበርካታ የዓለም አገራት ልምድ የሚወሰድበትና በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማሳተፍ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏ በስኬት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓደ አሻራ መርሃ-ግብር ዘንድሮም ቀጥሎ የሁለተኛው ምእራፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአፋር ክልል በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም