የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቋሙን በሰው ኃይል በማብቃት፣ በቴክኖሎጂ በማዘመንና ምቹ ከባቢን በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው - የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቋሙን በሰው ኃይል በማብቃት፣ በቴክኖሎጂ በማዘመንና ምቹ ከባቢን በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው - የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች
አዲስ አበባ ሰኔ 10/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቋሙን በሰው ኃይል በማብቃት፣ በቴክኖሎጂ በማዘመንና ምቹ ከባቢን በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አብራሪዎችና ሰራተኞች የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም አየር ሃይሉ ለታላቅ አገር ታላቅ ተቋምን የመገንባት ዓላማ አንግቦ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አየር ሃይሉ ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር አንጻርም ውጤታማ ሥራዎች ሰርቷል ብለዋል።
በአየር ኃይሉ አስደናቂ የሚባል ለውጥ መደረጉን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው አሰራሩን ከማዘመን አንጻርም ስኬታማ ሥራ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ብቃት ያለውን የሰው ሃብት በመገንባት እንዲሁም የሠራዊቱ አባላትም በይቻላል መንፈስ አመርቂ ሥራዎችን ማከናወን መቻላቸውን ለመመልከት ችለናል ብለዋል።
አየር ኃይሉ ኢትዮጵያን የሚጠብቅና የአገር ኩራት የሆነ ተቋም ደረጃ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።
አየር ሃይሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ የሆኑ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸው ለረጅም ዓመታት የቆሙ አውሮፕላኖችን በራስ አቅም ጠግኖ ለአገልግሎት በማብቃት ላይ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በጉብኝቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎችና ሰራተኞች በበኩላቸው አየር ሃይሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታላላቅ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት በሁሉም ረገድ ለአገር ኩራት በሚሆን ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመው ብቃት ያለውን የሰው ሃይል በማፍራት ላይ ስለመሆኑም መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አሰራሮቹን በማዘንም ረገድም ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም አየር ሃይሉ እየሰራቸው ባሉ የጥገና አቅም ማሳደግ፣ ቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ግንባታ ከራሱ አልፎ ለሌሎች አገራት የመትረፍ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
አየር ሃይሉ "ትልቅ አየር ሃይል ለታላቅ ህዝብ እና አገር" የሚለውን መለያውን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
ከራስ በፊት አገርን ማስቀደም ውጤታማ እንደሚያደርግ በጉብኝታቸው መረዳታቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው በተቋሙ የተወሰደው የለውጥ እርምጃ አገርን በችግር ውስጥም መገንባት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይልም አስተማማኝ የሰው ኃይልና ዘመናዊ ትጥቅ እንዲኖር በማድረግ እንዲሁም ተቋሙ ፅዱና ማራኪ እንዲሆን ያስቻለ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አብራሪዎችና ሰራተኞች በኢትዮጵያ አየር ሃይል ቅጥር ግቢ ውስጥ አርንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።