መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጉ የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ይረዳል - የቴሌኮም ዘርፍ አማካሪ ሚሼል ጉንታ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጉ የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ይረዳል - የቴሌኮም ዘርፍ አማካሪ ሚሼል ጉንታ
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015(ኢዜአ)፡- መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጉ የዘርፉን እድገት ለማስቀጠልና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የቴሌኮም ዘርፍ አማካሪው ሚሼል ጉንታ ገለጹ።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በመንግሥት ብቻ ሲቀርብ የነበረውን አገልግሎት ለዓለም አቀፍ አገልግሎት አቅራቢዎች ክፍት መደረጉ ይታወሳል።
በዚህም ነባሩ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ ሁለት አዳዲስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲኖሩ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቀጥሎ ሁለተኛውን አዲስ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ለመሥጠት ዝግጅት እያደረገ ነው።
ይህም የመንግሥት ውሳኔ የሚደነቅና ለዘርፉ እድገት በርካታ ጥቅሞች ይዞ እየመጣ መሆኑን ነው የዘርፉ አማካሪ ሚሼል ጉንታ ለኢዜአ የገለጹት።
ይህ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በማጋራት አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማስረጽ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እድልና ተስፋ ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በኩባንያዎች መካከል ውድድር እንዲዳብር ያስችላልም ነው ያሉት።
ይህም ደግሞ የቴሌኮም ዘርፍ ተደራሽነትን ለማስፋት እንደሚያስችል በመጠቆም።
ኢትዮጵያ አሁን እያደረገች ያለው የዲጂታል ሥርዓት ግንባታና የቴሌኮም ዘርፍ እንቅስቃሴ በአፍሪካ ወደ ላቀ ደረጃ የሚወስዳት መሆኑንም እምነታቸውን ገልጸዋል።
እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ሥርዓት ግንባታ ይበልጥ በማጠናከር የዘርፉን እድገት ማስቀጠል እንደሚገባ ምከረ ኃሳብ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቀጥሎ ሁለተኛውን አዲስ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት በያዝነው ሰኔ ወር ጨረታ እንደሚወጣ መግለጹ ይታወሳል።